በመቀሌ አሁን ላይ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ

66

አዲስ አበባ፤ ህዳር 24/2013 (ኢዜአ) የሀገር መከላከያ ሰራዊት የመቀሌ ከተማን ከተቆጣጠረ በኋላ በከተማዋ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ነዋሪዎች ተናገሩ።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከቀናት በፊት ሰላማዊ ዜጎችና ቅርሶችም ሳይጎዱ መቀሌ ከተማን መቆጣጠሩ ይታወሳል።

ከዚህ በኋላ ከተማዋ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተመልሳለች፣ ነዋሪዎች ወደ መደበኛ ስራቸው በመመለስ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚሉት፤ የህወሃት ቡድን "የመከላከያ ሰራዊቱ ከተማዋን ለማውደም የመጣ ነው" በማለት የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ሲሰራጭ ቆይቷለ።

ከዚህ የተሳሳተ ወሬ የተነሳም በርካቶች ስጋት ገብቷቸው እንደነበር ተናግረዋል።

ጁንታው ተባርሮ ሰራዊቱ ከተማዋን ከተቆጣጣረ በኋላ ግን አካባቢው ሰላም ሆኗል ነዋሪውም እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።

ሰራዊቱ ከእለት ጉርሱ ቀንሶ  በችግር ውስጥ ያሉ የከተማዋን ነዋሪዎች ሲመግብ መመልከታቸውንም ነዋሪዎቹ ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ ከተማዋ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሰችና ከእለት ወደ እለት ነዋሪዎች ወደ መደበኛ ስራቸው መመለስ ጀምረዋል ነው ያሉት።

 የከተማዋ ነዋሪዎች ከመከላከያ ሰራዊቱ ጋር በመሆን የአካባቢያቸውን ሰላም እየጠበቁ መሆኑንም ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ጊዜያዊ አስተዳዳሪ በህዝብ በማስመረጥ ላይ መሆናቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም