ምክር ቤቱ የፌዴራልና የክልል መንግስታት የግንኙነት ስርዓትን ለመወሰን የወጣውን ረቂቅ አዋጅ አፀደቀ

90

አዲስ አበባ፤ ህዳር 24/2013(ኢዜአ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራልና የክልል መንግስታት የግንኙነት ስርዓትን ለመወሰን የወጣውን ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምፅ አፀደቀ።

ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ ኒውክለርን አማራጭ የሃይል አቅርቦት ለማድረግ ከሩሲያ ጋር የተፈራረመችውን የስምምነት ረቂቅም በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ አካሂዷል።

በዚህም የፌዴራልና የክልል መንግስታት የግንኙነት ስርዓትን ለመወሰን የወጣውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።

ከሶስት ዓመታት በፊት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣው ረቂቅ አዋጅ በምክር ቤቱ የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና በሚመለከታቸው አካላት በጥንቃቄ ሲታይ እንደነበር ተገልጿል።

የፌዴራልና የክልል መንግስታት ያላቸውን አቅም በማቀናጀት ህጋዊ በሆነ መንገድ ለኢትዮጵያ ህዝቦች ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት እንዲሰጡ የግንኙነት ስርዓቱ ወሳኝ መሆኑ ተብራርቷል።

ረቂቅ አዋጁ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ አልዘገየም ወይ? የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የክልል መንግስታት በረቂቅ አዋጁ ላይ የነበራቸው ተሳትፎ ምን ይመስላል? የሚሉና ሌሎችንም ጥያቄዎች በምክር ቤት አባላት ተነስተዋል።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በኢትዮጵያ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት የፌዴራልና የክልል መንግስታት ግንኙነት ህጋዊ ዕውቅና ሊኖረው ይገባል ብለዋል።

በተናጠልና በጋራ የተሰጣቸውን ስልጣንና ተግባር በግልጽ በማስቀመጥ አገራዊ የልማት ስራዎችን በተናበበ መልኩ መስራት እንደሚገባቸውም ነው ያነሱት።

በኢትዮጵያ ቀደም ሲል የነበረው የአንድ ፓርቲ ስርዓት የመንግስት ስራ በህግ አግባብ ሳይሆን በመንግስታቱ በጎ ፍቃድ ብቻ እንዲመራ አድርጓል ብለዋል።

ይህም በፌዴራልና በክልሎች መካከል የተናበበ ውጤታማ ስራ እንዳይሰራ እንቅፋት ሆኗል ነው ያሉት።

ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁን ቀደም ሲል ሲያወጣቸው ከነበሩ ህጎች በተለየ ጊዜ ወስዶ በከፍተኛ ጥንቃቄ ማየቱንም አፈ ጉባኤው ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ ኒውክለርን ለሰላማዊ ዓላማ ተጠቅማ አማራጭ የሃይል አቅርቦቷን ለማስፋት ከሩሲያ መንግስት ጋር የፈረመችው ስምምነት ረቂቅ አዋጅንም በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

የኢትዮ-ሩሲያን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ አዲስ የሃይል አማራጭ ለመፍጠር ያስችላል ተብሏል።

በምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ የኒውክለር ስምምነቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አብራርተዋል።

የምክር ቤቱ የ6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ ልዩ ስብሰባ ቃለ ጉባኤም በሙሉ ድምጽ ጸድቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም