ለሰላም የተዘረጋን ክንድ የረገጠ እብሪት

91

በመንግስቱ ዘውዴ (ኢዜአ)

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ የዓለም የሰላም ኖቤል ሽልማት መቀበላቸውን ተከትሎ ጥቅምት 08 ቀን 2012 ዓ.ም በሚኒየም አዳራሽ “ሰላም መቶ በመቶ ያሸልማል” በሚል መሪ ሃሳብ የሰላም ሚኒስቴር አንድ መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። በመድረኩ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አምባሳደሮች፣ ኮር ዲፕሎማቲክ አባላትና የዓለም አቀፍ ተቋማት የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

"ኢትዮጵያ እንደ እናት ሆና በእኔ ውስጥ ያለማቋረጥ እንዲህ ትላለች ልጆቼ በተለያዩ አጋጣሚዎችና ምክንያት ከፍ ልታደርጉኝ ወድቃችሁ ተነስታችኋል። አንገቴን ቀና ማድረግ ጀምሬአለሁ፤ ነገር ግን ደግሞ በየመሀሉ ለበርካታ ጊዜያት አንገቴን  ታስደፉኛላችሁ፤ መደማመጥ ጠፍቶ አንዴ በብሔር አንዴ በሃይማኖት አንዴ በዚህ አንዴ በዚያ እርስ በርስ ተጎዳድተው ያጣኋቸው ልጆቼ ብዙ ናቸው፤ በቅርቡ በመካከላችሁ የማየውና የምሰማው ንትርክና ጥላቻ አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ መባባል ጠፍቶ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ መሆኑ እንቅልፍ እየነሳኝ ሰቀቀን ውስጥ ከቶኛል፤ በድህነት ተቆራምጄ የሰው ፊት እየገረፈኝ ያስተማርኳችሁ የፍቅር፣ የመከባበርና የአብሮነት፣ የልማትና የዴሞክራሲ በጥቅሉ የብልጽግና ድልድይ እንድትገነቡበት ነው፤  አንደበታችሁ የፍቅርና የመተሳሰብን ዝማሬ እንዲያስተጋባ እንጂ የጥላቻ መርዝን እንዲዘራ አይደለም።" በማለት የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በመክፈቻ ንግግራቸው ስለሰላም አስፈላጊነት አጽንኦት የሰጠ መልእክት አስተላልፈዋል። 

በአገራችን በተለያዩ ጊዜያት የሰላም መደፍረስ ያጋጠመ ቢሆንም ባለፉት ሁለት ዓመታት የታየው ሁኔታ ግን ከተለመደው ወጣ ያለ ነበር። ባለፉት ሁለት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል ቡራዩ፣ ሻሸመኔ፣ ባሌ፣ ጉጂ፣ ሃረርጌ፣ ወለጋን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ከፍተኛ ግጭት ተከስቷል። በኦሮሚያ ክልል ብቻ 37 ግጭቶች ተፈጥረዋል፡፡ በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 15፣ በአዲስ አበባ 14፣ በአማራ ክልል 23 እንዲሁም በድሬዳዋ፣ በሲዳማ፣ በጉራፈርዳ እና በሌሎች አካባቢዎች የተለያዩ አይነት ግጭቶች ተፈጥረዋል። እነዚህ ግጭቶች በባህሪያቸው ብሔርን ከብሔር ጋር ወይም ኃይማኖትን ከኃይማኖት ጋር እንዲጋጩ የሚያደርጉ ነበሩ። በዚህም በርካታ ንፁሃን ዜጎች ላይ ጉዳት ደርሷል፤ ብዙዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ ንብረትም ወድሟል።

ሀገራዊ ለውጥን ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭት እንዲቀሰቀስና ሀገሪቱ እንዳትረጋጋ በማድረግ ረገድ ዋነኛ ተዋናይ የነበረው የህወሃት ጽንፈኛው ቡድን ስለመሆኑ መንግስት በተደጋጋሚ አሳውቋል።  ህወሃት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እርስ በርስ እንዳይተማመኑ በማድረግ አንዱ በሌላው ላይ ጥላቻና ቂም እንዲይዝ ሲያደርግ የቆየ ስለመሆኑ ብዙዎች የሚናገሩ ቢሆንም ከሁለት ዓመት ወዲህ ግን የጥፋት ቡድን አስመስክሯል።   

የህወሃት የጥፋት ቡድን በግልጽ እየታየ መምጣት የጀመረው ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የኢህአዴግ ሊቀመንበር እና በኋላም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተመረጡበት ጊዜ ጀምሮ ነው። በሙስናና ብልሹ አሰራሮች ምክንያት በሀገር አቀፍ ደረጃ መንግስትን በመቃወም ህዝባዊ አመጽ መቀስቀሱን ተከትሎ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው በመልቀቃቸው የፓርቲው ስራ አስፈፃሚዎች ባደረጉት ስብሰባ ዶ/ር ዐብይ አህመድን የፓርቲው ሊቀመንበር በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል።የህወሓት የጥፋት ቡድን የኢህአዴግ ሊቀመንበር ምርጫ ከመካሄዱ ጥቂት ሳምንታት በፊት በለውጥ ሃይሉ ላይ የእስር ትዕዛዝ እስከማውጣት ደርሶ እንደነበር ይነገራል።

የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ባካሄደው ተከታታይ ስብሰባ የፓርቲው ሊቀመንበር ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ስነስርዓት ተካሂዶ በብዙ ክርክርና ውዝግብ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ከፍተኛ ድምጽ በማምጣት የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል።የለውጥ ኃይሉ ስልጣን ከተረከበ በኋላ ከህወሓት የጥፋት ጋር በይቅርታ እና ያለፈውን በደል ላለማንሳት ከመወሰኑም ባሻገር በአገር ውስጥና በውጭ ያሉትን ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በቀረበው ጥሪ ታሪካዊ በሚባል ደረጃ ለረጅም ዓመታት በስደት የኖሩትን ጨምሮ ብዙዎች ወደ አገራችን ተመልሰዋል።

አብዛኛው የህወሃት የጥፋት ቡድን ከፌዴራል መንግስት የስልጣን ቦታዎች በመልቀቅ ወደ መቀሌ የመሸገው ኢህአዴግ ፈርሶ ከአጋር ፓርቲዎች ጋር ውህደት በማድረግ የብልጽግና ፓርቲ ሲመሰረት ነው። ይህ የውህደት አጀንዳ አዲስ የተፈጠረ ሳይሆን የቀድሞው የኢህአዴግ ሊቀመንበር አቶ መለስ ዜናዊ በስልጣን ላይ እያሉ የተጀመረ እንቅስቃሴ እንደነበር የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በቅርቡ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል። በአቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ የስልጣን ዘመንም አጀንዳው በጥናት ላይ እንዲመሰረትና በፍጥነት እንዲተገበር አቅጣጫ ተቀምጦለት ነበር። ጉዳዩ በተለያዩ ጊዜያት ውይይት ሲካሄድበት የቆየ ሲሆን ከህወሃት በኩል አንድም ጊዜ የተቃውሞ ሃሳብ ተነስቶ እንደማያውቅ በዚሁ ማብራሪያቸው አክለው ገልጸዋል።፡

የለውጡ አመራር ስልጣን በተረከበበት ወቅት ቀደም ሲል ሲካሄድ በቆየው ጥናት የአራቱ ድርጅቶች ሊቀ-መናብርትና ምክትል ሊቀ-መናብርት የተሳተፉበት ዎርክ ሾፕ ተዘጋጅቶ ያለምንም ልዩነት ከተስማሙ በኋላ አፈጻጸሙ እንዴት ይሁን በሚለው ላይ ተጨማሪ ጥናት እንዲደረግ ተስማምተው መለያየታቸውን በተለያዩ መድረኮች ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ የውህደቱ አስፈላጊነት በተመለከተ፤ በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ቤተኛ እና ባይተዋር የሆኑ አካላትን ላለመፍጠር፤ ለመሃል ሀገር ሩቅ የነበሩ ክልሎችና የህብረተሰብ ክፍሎች ተካተው ውሳኔ ሰጭ እንዲሆኑ ለማድረግ፤ በተጨማሪም ፌዴራሊዝሙ እውነተኛ ፌዴራሊዝም እንዲሆን ለማድረግ ያለመ መሆኑ ገና አጀንዳው ሲቀረጽ ጀምሮ የተግባቡበት ጉዳይ ነበር፡፡  

የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በሰጡት ማብራሪያ በ2008 ዓ.ም የውህደቱ ጥያቄ የአመራር እና የአባላት ፍላጎት ስለመሆኑ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የተጠናው ጥናት ግኝት ማሳየቱን ገልጸዋል። ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው በተመረጡበት ወቅት በጥናቱ ግኝት ላይ ለመምከር የአራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበር የተሳተፉበት ወርክሾፕ ተዘጋጅቶ በጥናቱ ግኝት ላይ ውይይት በማድረግ ቀጣይ አፈፃፀሙን በተመለከተ ተጨማሪ ጥናት እንዲካሄድና ቀደም ሲል ጥናት ያካሄዱ ምሁራን የአፈፃፀሙን ሂደት እንዲያቀርቡ ተደረገ። ምሁራኑ ጥናት አካሂደው ባቀረቡት ዝርዝር የአፈፃፀም ሂደት ዙሪያ በድጋሚ ውይይት መደረጉንም ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ገልጸዋል። በተጨማሪም የጥናቱ ግኝት ላይ የማሰላሰያ ጊዜ እንዲኖር በመታሰቡ የ3 ወር ጊዜ ተሰጥቶ በየማእከሉ ሰፋፊ ውይይቶች ተካሂደዋል። ጥናቱን ያካሄዱ ሙያተኞች በተገኙበት መነሳት ያለባቸው ጥያቄዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል ብለዋል። 

በዚህ ወቅት አንዳንድ አካላት “ለምን እንዲፈጥን ተፈለገ?” የሚሉ ጥያቄዎች ይነሱ እንደነበር ወ/ሮ ሙፈሪያት ጠቁመው 12 ዓመታት በጥናት፣ በምክክርና በውይይት ሲብላላ የሰነበተ ጉዳይ እንዴት ተቻኮለ ተብሎ ይጠየቃል? ይላሉ። ከዚሁ ጋር አያይዘው ለውጥ ባለንበት የሚቆም እንዳልሆነና በፍጥነት ወደፊት መጓዝን እንደሚጠይቅ በመግለጽ አንዳንድ ሰዎች ከእውነት ጋር መታረቅ የሚቸግራቸው ተናግረዋል። እናም መነሳት የነበረበት ውህደቱ እስካሁን ለምን ዘገየ? የሚል ጥያቄ እንጂ ተቻኮለ የሚለው ተቀባይነት ያለው ሃሳብ አለመሆኑን በዚሁ ገለጻቸው አስረድተዋል።

የውህደቱን አይቀሬነት የተረዳው ህወሃት መቀሌ በመሄድ ማዕከላዊ ኮሚቴውንና አጠቃላይ አባላቶቹን አወያይቶ ውህደቱን እንደማይቀበል በግልጽ አቋሙን አሳውቋል። ህወሃት በመግለጫው “በሁሉም መለኪያዎች አንድ ፓርቲ ለመሆን የሚያስችል መነሻና ምክንያት በሌለበት ኢህአዴግን አፍርሶ ሌላ ፓርቲ ለማቋቋም ማሰብ አገርን የሚበትን ተግባር ነው” ሲል ጉዳዩ የሞት ሽረት መሆኑን አስታውቋል። በተለያዩ ቦታዎች ግጭት እየተባባሰ የሄደውም በዚሁ ምክንያት ነው ሲል አክሎ ገልጿል። ይህን ተከትሎ በመንግስት በኩል ውህደቱ ህወሃትን ጨምሮ የትግራይ ህዝብንም የሚጠቅም መሆኑን ለማስረዳት የተለያዩ ሙከራዎች መደረጉን ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

በዚህ ጊዜ ቀድሞ በከፍተኛ አመራርነት ቦታ ላይ የነበሩ ሰዎች ከመስመሩ መውጣት ሲጀምሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ እባካችሁ መልሷቸው ሀገራቸው ነው ማንም አይነካቸውም” የሚል የልመና ያህል ጥያቄ አቅርበው እንደነበርና በርካታ ሰዎች በቃ መለማመጥ አያስፈልግም እስከማለት ተደርሶ እንደነበር የሰላም ሚኒስትሯ በቅርቡ አብራርተዋል።

የለውጡ አመራር የህወሃት አመራሮች ባጠፉት ጥፋት ልክ ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ ለበርካታ ዓመታት የሀገራችን አክሳሪ የፖለቲካ ልምምድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መቋጨት እንዲቻል ካለው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ ለውጡን እንዲቀላቀሉ ጥረት እንዳደረገ ነገር ግን ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ከተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡ ነባሮቹን አመራሮች አቅፎ በመሄድ ሊገኝ የሚችለውን አዲስ የዲሞክራሲ ልምምድ ለማዳበር ሲል እንደ አቶ አባይ ጸሀዬ፣ አቶ በረከት ስምኦን፣ አቶ ስብሃት ነጋ፣ አምባሳደር ስዩም መስፍን ሌሎቹም ያላቸውን ልምድ እና ዕውቀት ተጠቅመው ለውጡን እንዲደግፉ ለማድረግ መንግስታዊ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው እንደነበር በሂደቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩት ወ/ሮ ሙፈሪያት ተናግረዋል። 

በተጨማሪም ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሲሉ ከዶ/ር ደብረጺዮን ጋር እንዲሁም ከሌሎች አመራሮችና ከትግራይ ተወላጅ የንግዱ ማህበረሰብ አካላት ጋር ሁሉ ችግሩ እስከተፈጠረበት ምሽት ድረስ ተደጋጋሚ ውይይቶች እየተደረጉ እንደነበር የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በተጨማሪም በመቀሌና በአክሱም ከተሞች ከህዝቡና ከህወሃት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በተደረጉ ውይይቶች ክልሉን እያስተዳደረ ያለው ህወሃት የህዝቡን ችግር በዘላቂነት መፍታት በሚያስችሉ የልማት ስራዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ፤ ህዝቡም ለስኬታማነቱ እንዲተባበር፤ በዚህም የፌዴራል መንግስት ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በህዝብ ተወካዮችና በልዩ ልዩ የውይይት መድረኮች ሁሉ ሳይቀር ህወሃትና ጥቂት ደጋፊዎቹ ለውጡን እንደ ዕድል በመጠቀም በጋራ እንዲሰሩ፣ ካልተገባና አገር አፍራሽ ከሆነ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ከሚደረግ እንቅስቃሴያቸው እንዲታቀቡ በተደጋጋሚ ምክር እንደለገሱ ይታወቃል፡፡ ከዚህም አልፎ የክልሉ አስተዳደር በራሱ አቅም መፍታት ያልቻላቸውን እንደ የመቀሌ ውሃ ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ፣ ከህግና ከአሰራር ወጣ ባለ መልኩም ቢሆን የቀድሞ የህወሃት ታጋዮችን ጡረታ ለማስከበር እና ህይወታቸውን ለመቀየር የሚያስችሉ ጥረቶች ስለመደረጋቸው በተደጋጋሚ ተገልጿል።  

አዲሱ የለውጥ አመራር ቀድሞ የነበረውን አግላይና ገፊ የፖለቲካ አሰራር ላለመድገም ጥረት ቢያደርግም ይህንን መቀበል አለመፈለጋቸው ህዝብም፣ መንግስትም፣ ራሳቸውም ጭምር ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍሉ አድርጓል ሲሉ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡

የህወሃት ከውህደት ማፈንገጥን ተከትሎ በሀገሪቱ እየተከሰቱ የነበሩ ችግሮች በፌዴራል መንግስቱ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎች፣ ድጋፎችና ማሳሰቢያዎች እየቀነሱ መምጣት ሲገባቸው እየጨመሩ ሄዱ፡፡ በዚህ ወቅት ነበር የፌዴራል መንግስቱ በቃል ከማሳሰብ ባለፈ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ወደ ሚያስችሉ ተጨማሪ የሰላም አማራጮች የተሸጋገረው፡፡ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶችም ጉዳዩን ለመፍታት የራሳቸውን ጥረት አድርገዋል።

የህወሃት ልክ ያልሆነ አካሄድ እያደረሰ ያለው ሀገራዊ ጥፋት ከፍተኛ እየሆነ በመምጣቱ የትግራይ ክልልን ጨምሮ በበርካታ ክልሎችና አካባቢዎች የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በዘላቂነት መፍታት እንዲቻል ሀገር በቀል የችግር መፍቻ ዘዴዎችን መጠቀም ተገቢ እንደሆነ በፌዴራል መንግስት ታመነበት፡፡ በዚህም በሀገር ደረጃ ያሉ ችግሮችን በማጥናት በእርቅ እንዲፈታ፤ ከመንግስት ጣልቃ ገብነት በጸዳ መልኩ ስራዎችን የሚሰራ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን እንዲቋቋም መደረጉን በመንግስት የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት መማክርት ጉባኤ እና የሃገር ሽማግሌዎች ወደ መቀሌ በመጓዝ በወቅቱ ከነበሩ የክልሉ አመራሮች ጋር በሰላም ዙሪያ ውይይት ያደረገ ቢሆንም በክልሉ መንግሥት በኩል “በአሁኑ ጊዜ ያለው ችግር ሀገራዊ በመሆኑ መፈታት የሚገባውም ሁሉንም የሃገሪቱ ክፍሎች ባካተተ መልኩ ነው” የሚል ምላሽ ተሰጥቷል።

የሀገር ሽማግሌዎቹ በሁለቱ አካላት መካከል የተፈጠረውን ችግር በሰላማዊ ውይይትና ድርድር እንዲፈቱ ለማግባባት ወደ መቀሌ በሄዱበት ወቅት እስካሁን ድረስ የት ነበራችሁ፤ የሚያስፈልገው እርቀ ሰላም አይደለም በማለት ከክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ያገኙት ምላሽ በጣም አሳዝኗቸው እንደነበር በቅርቡ ለተለያዩ  መገናኛ ብዙሃን አስተያየታቸውን የሰጡ የጉባኤው አባላት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

ይህም ህወሃት ቀድሞውንም ችግሮችን በሀይልና በሴራ ካልሆነ በቀር በሰላማዊ መንገድና በዕርቅ መፍታት ልምዱም߹ ፍላጎቱም፣ ሞራላዊ ብቃቱና ባህሪው ስላልሆነ ጉባኤው የተቋቋመበትን ሂደቶች ሁሉ አጣጥሎ በጊዜው በንግግር ከዛም በተግባር እንደማይቀበለው እንዳስታወቀ ተገልጿል፡፡

ከዚህ በኋላም ህወሃት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሀገራዊው ምርጫ እንዲራዘም ያሳለፏቸውን ውሳኔዎች እንደማይቀበል መግለጹን ተከትሎ፤ መንግስት የትግራይ ክልል መንግስት የምክር ቤቶችን ውሳኔ እንዲያከብርና ለህግ ተገዢ እንዲሆንም አሳስቦ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ሰኔ 2012 ዓ.ም መጀመሪያ ቀናት አካባቢ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ህወሃትን ጨምሮ ለሌሎቹም የፖለቲካ ፓርቲዎች ባስተላለፉት መልዕክት ላይ ያለችን አንድ ሀገር መሆኗን ተረድታችሁ ልዩነቶችን በሰከነ አግባብና በሰለጠነ ውይይት እንድንፈታ” ሲሉ ጥሪ አቅርበው እንደነበር ይታወሳል። በተመሳሳይ በ2013 ዓ.ም አዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ ህወሓት የፌዴራል መንግስት የሀይል አማራጮችን እንዲወስድ ከሚያነሳሱ ትንኮሳዎች መታቀብ አለበት ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ህወሃት የሰላምን መንገድ ወደ ጎን በመተው በክልሉ ያለው የመከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ አባላት ለስራ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንቅፋት መሆን፤ የሰራዊቱ አባላት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ወቅት ያልተፈለገ ፍተሻ በማድረግ ከፍተኛ እንግልት መፍጠር፤ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ አዛዥን በመቀሌ በማገት ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ በማድረግ የፌዴራል መንግስትን ትዕግስት መፈታተኑን አላቆመም። 

የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም በክልሉ ሚዲያ በኩል በሰጡት መግለጫ ጦርነት ትግራይ ላይ እንደማይቀርና ህዝቡ እንዲዘጋጅ ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን ወደ ትግራይ የሚመጡ ማናቸውንም አካላት እንቀብራቸዋለን” እስከማለት የደረሰ ጠንካራ ንግግር አድርገዋል። አዲሱን ዓመት በማስመልከተ መልእክት ባቀረቡበት ወቅትም “የትግራይ ህዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የማስተዳደር መብቱ የራሱ በመሆኑ የህዝቡን ውሳኔ ከመቀበልና ከማክበር ውጭ ሌላ አማራጭ ማሰብ የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች ያስከትል እንደሆነ እንጂ ሌላ ፋይዳ የለውም” ሲሉ ተደምጠዋል።

ህወሃት በተደጋጋሚ የቀረበለትን የሰላም ጥሪ በመርገጥ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ አባላት ላይ ጥቃት በማድረስ የሀገር ክህደትን ፈጸመ። ጥቃት ስለመፈጸሙም የቡድኑ አፈቀላጤ የሆኑት አቶ ሴኮ ቱሬ ጌታቸው ጀብደኝነት በተሞላበት አንደበት በክልሉ ሚዲያ በይፋ ተናገሩ። ህወሃት የእናቱን ጡት ነከሰ፤ ቀዩን መስመር አለፈ፣ የሰላም ጥሪውም ዋጋ ቢስ ሆነ። በከፍተኛ ትዕግስት ለበርካታ ጊዜያት፣ በተደጋጋሚና በተለያዩ አካላት ለማሳካት የተሞከረው የሰላም ጥሪ ፋይል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተዘጋ።

አንዴ ከተመዘዘ ለመመለስ ከባድ የሆነውና ክንዱ ልክ እንደ ፍም ረመጥ የሚፋጀው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት በክህደትና በደል ፈጻሚው የህወሃት ጁንታ ላይ በወሰደው እርምጃ የትግራይን ክልል ሙሉ በሙሉ ነፃ አውጥቷል። በሽምግልና ወይም በድርድር ሲደረግ የነበረው ተማጽኖ አሻፈረኝ ያለው የህወሃት ጁንታ ተገዶ በህግ ተጠያቂ የሚሆንበት ምእራፍ ላይ ተደርሷል። ቀጣዩ ሥራ ክልሉን የማረጋጋት፣ ልማትን የማፋጠንና አጥፊውን ለህግ አቅርቦ ፍርድ መስጠት ይሆናል። ሰላም!!!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም