የህወሓት የጥፋት ቡድን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተልዕኮ ጦርነት ሲፈጽም ነበር-ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል

51

አዲስ አበባ፣ ህዳር 23/2013(ኢዜአ) የህወሓት የጥፋት ቡድን ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተልዕኮ ጦርነት ሲፈጽም እንደነበር የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ተናገሩ።

የሰላም ሚኒስቴርና በሥሩ ያሉ ተጠሪ ተቋማት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአንደኛ ሩብ ዓመት ሪፖርትን ዛሬ ሲያቀርቡ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት እንዳሉት ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል ጊዜያት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ተከስተዋል።

በዚህም በርካታ ንጹሀን ዜጎች ለሞትና ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን አስታውሰው፣ "በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን የተልዕኮ ጦርነት ሲፈጽም ነበር" ብለዋል።   

መንግስት በየአካባቢው ሲፈጠሩ የነበሩ ችግሮችን ከመፍታት በተጨማሪ መዋቅራዊ የሆኑ ጉዳዮችን ለማስተካከል ሲሰራ መቆየቱን አመልክተው፣ ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም የአቅም ግንባታና የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን ከመስጠት ባለፈ ውይይቶችን ማድረግና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የተሰራውን ስራን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የግጭትና የሰላም ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት በየጊዜው ሲሰራ እንደነበር ገልጸው፣ "ለዚህም ምሁራንን በማሳተፍ ችግሮችን በጥናትና በእውቀት ለመፍታት ጥረት ተደርጓል" ብለዋል።

የህወሓት የጥፋት ቡድን ወደ ህግ ሲቀርብ በኢትዮጵያ የተሻለ ጊዜ ይመጣል የሚል ጽኑ እምነት እንዳላቸው ጠቁመው የህግ ማስከበር ስራውን ተከትሎ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ በበኩላቸው የህወሓት ጁንታ በአገሪቱ በየጊዜው ለተከሰቱ ግጭቶች  መሳሪያ በማስታጠቅና በገንዘብ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።

"በዚህም የጥፋት ቡድኑ በአገሪቱ በህዝቦች መካከል ግጭት እንዲፈጠርና በንብረት ላይ ውድመት እንዲደርስ አድርጓል" ነው ያሉት።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልሎች እንዲሁም በቅርቡም በማይካድራና በሌሎችም አካባቢዎች ግጭት ሲፈጥር የነበረው ይህ ቡድን መሆኑን በማስረጃ አረጋግጠናል ሲሉም አክለዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ የሰላም ሚኒስቴር በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እያደረገ ያለውን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጠል አሳስበዋል።

በህወሓት የጥፋት ቡድን የህግ ማስከበር ስራ በተሰራባቸው አካባቢዎች ዜጎችን የማረጋጋት ሥራ በተጠናከረ መልኩ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ጽንፈኛው ቡድንና ተላላኪዎቹ ሌሎች መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ህብረተሰቡን እያሳሳቱ በመሆኑ በተጨባጭ ለህዝቡ ያለውን እውነታ በየጊዜው ማሳወቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከቋሚ ኮሚቴው የተሰጠውን ግብረመልስ በመውሰድ በቀጣይ ለማሻሻል መስራት ይጠበቅበታል ሲሉም አሳስበዋል።

የቋሚ ኮሚቴው የሰላም ጉዳይ ንዑስ ሰብሳቢ ወይዘሮ ብርቱካን ሰብስቤ በበኩላቸው የግጭቶችን ምንጭ በወቅቱ ለመለየት የተደረገ ሥራ ዝቅተኛ በመሆኑ በቀጣይ ትኩረት ይደረግበት ብለዋል።

የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል መስሪያ ቤታቸው የተሰጠውን ግብረመልስ በመቀበል ለቀጣይ የተሻለ ስራ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም