ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያላቸውን ፍቅር በተግባር ማሳየታቸውን አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ

110

ሐረር፣ ህዳር 23/ 2013 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶክተር አብይ አህመድ የገጠማቸውን ፈተና በማለፍ ለኢትዮጵያ ህዝብና መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ፍቅር በተግባር እንዳሳዩ በሚገባ መረዳታቸውን በሐረር ከተማ አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ።

አስተያየት ሰጪዎቹ ለኢዜአ እንዳሉት ጁንታው ህወሃትና ተከታዩ ኦነግ ሸኔ በሽብርተኝነት መፈረጅ አለባቸው።

በከተማዋ የቀበሌ ስምንት  ነዋሪ ወጣት እያሱ ተሰማ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተወካዮች ምክር ቤት  የሰጡትን ማብራሪያ  በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት መከታተሉን ተናግሯል።

ከእሳቸው ማብራሪያ  የህወሃት ቡድን ሴራ  በተለይ በሰሜን ዕዝና በማይካድራ ንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸማቸው ዘግናኝ ተግባር ይበልጥ መገንዘቡን  ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡበት ሁኔታ እጅግ አስደስቶኛል ብሏል።

በተለይ  የምክር ቤቱ አባላት በሁሉም አካባቢ ዜጎች ላይ ግፍ የፈጸሙት ህወሃትና ተከታዩ ኦነግ ሸኔ  በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ ያቀረቡትን ሀሳብ  እንደሚደግፍ ተናግሯል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ በጣም ነው የኮራሁት፤ ትዕግስት ፍሬዋ ጣፋጭ መሆኗንና የት ቦታ እንደምትደርስ አሳይተውናል፤ በዚህም ተደስቼያለሁ  ያሉት ደግሞ አቶ በከር ሻሚ ናቸው።

ህወሃትንና ኦነግ ሸኔን በአሸባሪነት እንዲፈረጁ የምክር ቤቱ አባላት የጠየቁት አግባብነት  ያለው በመሆኑ እንደሚደግፉት ተናግረዋል።

ወይዘሮ መሰረት በቀለ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ  በትግዕስት እየመሩ  በሀገሪቱ ለውጥ  ለማምጣት ብዙ ውጣ ውረድ   እንዳሳለፉ ለምክር ቤቱ ከሰጡት ማብራሪያ በሚገባ መረዳታቸውን ገልጸዋል።

ባሳዩት ትዕግስት  ከእሳቸውም ብዙ ትምህርት ማግኘት ችያለሁ ብለዋል።

በተለይ ጁንታው በሰሜን እዝና ንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸመው የግፍ ወንጀል ከአሸባሪነት በላይ መፈረጅና መጠየቅ እንዳለበት ያመለከቱት አስተያየት ሰጪዋ ይህ እንዲፈጸም የምክር ቤቱ አባላት መጠየቃቸው ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ  ልብ የሚነካ ፣ብዙ ውጣ ውረድ የነበረበትና ስቃይ አይተው እዚህ መድረሳቸውን ተገንዝቤያለው ያሉት ደግሞ አቶ አበራ ደምሴ ናቸው።

ውጣ ውረዱንና ፈተናውን  ችለው በማለፍ ለኢትዮጵያ ህዝብ  ያላቸውን ፍቅር በተግባር በማሳየታቸው  ታላቅ  ክብር እና ምስጋና እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የጁንታው ተላላኪዎች  የጥፋት ድርጊት እንዳይፈጽሙ የመቆጣጠሩ ሥራ መጠናከር እንዳለበትም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም