መንግስት በትግራይ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ በሚደረግበት ሁኔታ ላይ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እየሰራ ነው - የሠላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል

65

አዲስ አበባ፣ ህዳር 23/2013 (ኢዜአ) መንግስት በትግራይ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ በሚደረግበት ሁኔታ ላይ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ የሠላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።

“ወደ ሱዳን የተሰደዱ ንጹሃን ዜጎችን የመመለስና የማቋቋም ስራ ይሰራል” ብለዋል።

የሠላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ለአውሮፓ ሕብረት የቀውስ ጊዜ አስተዳደር ኮሚሽን ኮሚሽነር ያኔዝ ሌናርቺች ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ ለማመቻቸት እያከናወነቻቸው ባሉ ተግባራት ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል።

በገለጻቸው መንግስት ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የሕወሓት ቡድን በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በሚያስነሳቸው ግጭቶች ምክንያት ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ በርካታ ዜጎችን የመመለስና የማቋቋም ስራ መሰራቱን አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት ወደ ሱዳን የተሰደዱ ዜጎችን ለመመለስና ለማቋቋም የልምድ ማነስ እንደሌለ ገልጸዋል።

ከተሰደዱት መካከል ማንነትን መሰረት ባደረገ ጭፍጨፋ እጃቸው ያለበት ተጠርጣሪዎች ሊኖሩ እንደሚችሉና ጉዳዩን የማጣራት ስራ እንደሚከናወን የማሳወቅ ስራ መሰራቱን ገልጸው፤ ዜጎችን ያከበረና ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የመመለስ ተግባር እንደሚከናወን ጠቅሰዋል።

የአውሮፓ ሕብረት የቀውስ ጊዜ አስተዳደር ኮሚሽነር ያኔዝ ሌናርቺች በበኩላቸው የሕግ ማስከበር ዘመቻውን ተከትሎ ወደ ሱዳን ለተሰደዱ ኢትዮጵያዊያን አራት ሚሊዮን ዩሮ መመደቡንም አመልክተዋል።

የአውሮፓ ሕብረት በስደተኞች ጉዳይ ላይ ላለፉት በርካታ ዓመታት ከመንግስት ጋር እየሰራ መሆኑንና የሚያደርገው ድጋፍም አውሮፓ ያላትን አጋርነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

በሠላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በተሰጣቸው ማብራሪያ ያለውን ሁኔታ መረዳት እንደቻሉ ገልጸው፤ በሱዳን በሚኖራቸው ቆይታ ስደተኞቹን እንደሚጎበኙና በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር እንደሚመክሩ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም