አባቶች ገብተው በአንድ ሲኖዶስ ቤተክርስቲያኒቱ የምትመራበት ሁኔታ ይፈጠራል-የዕርቀ ሰላም ልዑክ ቡድን

78
አዲስ አበባ አምሌ11/2010  በአገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች ጋር እርቅ ለመፍጠር የሚሰራው ልዑክ ሰላሙን አውርደው  ቤተክርስቲያኒቱ በአንድ ሲኖዶስ የምትመራበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ገለጸ። በሁለቱ ወገኖች መካከል ሰላም ለማውረድ ከ16 ወራት በፊት የተቋቋመው የእርቀ-ሰላም አስተባባሪ ልዑክ ለመጨረሻ ጊዜ ወደ አሜሪካ ጉዞውን ከማድረጉ በፊት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር መክረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ልዑኩ በትዕግስትና በአስተዋይነት ተልዕኮውን እንዲያከናውን መክረዋል። የእርቀ-ሰላሙ ልዑክ አባል አቡነ አብርሃም እንደገለጹት፤ ልዑኩ ወደ አሜሪካ አቅንቶ የቀድሞው ፓትሪያሪክና ከእሳቸው ስር ያሉ አባቶች ወደ አገር እንዲገቡና ቤተክርስቲያኗ በአንድ ሲኖዶስ የምትመራበት ሁኔታ ይፈጠራል። ሌላው የልዑኩ አባል ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ በውጭ ያሉ የቤተክርስቲያኗ አባቶች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ችግሩን ተነጋግረው የሚፈቱት መሆኑን አመልክቶ ችግሩ ሊፈታ ጫፍ ላይ መድረሱን ጠቁሟል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በሁለቱ መካከል እርቅ እንዲፈጠር ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እያደረጉት ላለው እገዛም አመስግኗል። የልዑኩ አባል የሆኑትና በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ምክር ቤት የአፍሪካ ተወካይ ዶክተር ንጉሱ ለገሰ እርቅና ሰላም ለማምጣት በሁለቱም በኩል በቅርበት መረጃ በመለዋወጥ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል። በውጭ አገር ያሉ አባቶች እርቅ ለማውረድ ፈቃደኝነት እንዳላቸው የሚያመላክቱ ሁኔታዎች መኖራቸውን ጠቁመው ልዑኩ ወደ አሜሪካ ሲሄድ የተለየ ችግር እንደማይገጥመው ተስፋቸውን ተናግረዋል። መንግስትም ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እያደረገላቸው እንደሆነ ጠቁመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ዛሬ የእርቀ ሰላም ልዑኩ ወደ አሜሪካ ሄዶ በስደት ላይ የሚገኙ አባቶች ወደ አገር እንዲገቡ መንግስት የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ እንደሆነም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም