ድህረ ለውጡ እና የህወሃት ጁንታ ተቃርኖ

140

በመንግስቱ  ዘውዴ  (ኢዜአ) 

በህወሃት የበላይነት ኢትዮጵያን ከ27 ዓመታት በላይ ሲያስተዳድር የነበረው ኢህአዴግ መራሹ መንግስት በሰብአዊ መብት ጥሰት፣ በሙስናና ብልሹ አሰራሮች በህብረተሰቡ ጠንካራ ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል። በእነዚህ ዓመታት በአስተዳደሩ ላይ ጠንካራ ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩትን የፓርቲ አመራሮች፣ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ለእስር ተዳርገዋል።

በዚህ ጊዜያት በኢህአዴግ ስም የህወሃት የአገዛዝ ዘመን የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግፍና ጭቆና ደርሶባቸዋል። በፖለቲካው መስክ ቁልፍ የስልጣን ቦታዎችን በመቆጣጠር እንዳሻው ለመምራትና ሌሎችን ለማሸማቀቅ ተጠቅሞበታል። የሀገሪቱ ሀብት በባለስልጣናቱ ሲመዘበር ሌላኛው ወገን ግን ሀብቱን እየተነጠቀና እየተዘረፈ ነበር። በማህበራዊ መስክም ቢሆን እርስ በርስ ከመተማመንና ከመደጋገፍ ይልቅ በዘረኝነት ተከፋፍሎ በጥርጣሬ እንዲተያዩና እንዲገፋፉ የሚያደርጉ ትርክቶች በተደጋጋሚ በማስረጽ እስከመጠፋፋት የሚያደርስ ክስተት እንዲፈጠር አድርጓል።      

የዴሞክራሲ ምህዳሩ ከጊዜ ወደጊዜ እየጠበበ ከመምጣት አልፎ ጨርሶ የተዘጋበት ምእራፍ ላይ ደርሶ ነበር። ሀገሪቱ የምትከተለው የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ቢሆንም ተአማኒነት በጎደለው የምርጫ ሂደት ምክንያት ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲገለሉ ተደርገው ገዥው ፓርቲ በተደጋጋሚ የፓርላማውን መቀመጫ ብቻውን እየተቆጣጠረ በመምጣቱ ራሱን “አውራ ፓርቲ” እስከማለት የደረሰበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

ይህም ብቻ ሳይሆን ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ በአገሪቱ የሚገኙትን ሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች በእኩልነት እንዲሳተፉ እድል መስጠት ተስኖት ከትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ውጪ ያሉትን አምስት ክልሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በአጋር ፓርቲነት በመፈረጅ የበይ ተመልካች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። አራቱን ክልሎች ከሚወክሉት ውጪ ያሉትን ማህበራዊ መሰረታቸው አርሶ አደር አይደለም በሚል ውሃ የማይቋጥር ምክንያት የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ  በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ በውሳኔ ሰጪነትም ሆነ በመሪነት ቦታዎች ላይ በቀጥታ ተሳታፊ አልነበረም፡፡

በህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን በዜጎች ላይ ይደርስ የነበረው እንግልት መሻሻል ከማሳየት ይልቅ ተባብሶ ቀጥሏል። ዜጎች በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ለእስር ተዳርገዋል፤ ብዙዎች ደግሞ አገር ለቀው ተሰደዋል። ጠንካራ ትችት የሚያቀርቡ ጋዜጠኞች ወህኒ ወርደዋል። በሌላ መልኩ ሙስናና ብልሹ አሰራር ተባብሶ ከመቀጠሉም በላይ የኑሮ ውድነቱ እጅግ እየናረ በመምጣቱ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል የእለት ጉርሱን የማያገኝበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ወጣቶች ለሥራ አጥነት በመዳረጋቸው በርካቶች እንጀራ ፍለጋ ስደትን አማራጭ አድርገዋል፤ በተሰደዱበትም ለመከራና ስቃይ ተዳርገዋል።

እነዚህ ነባራዊ ሁኔታዎች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ አድርገዋል። ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግም ብልሹ አሰራሮቹን አስተካክላለሁ በሚል ተደጋጋሚ ግምገማዎችን ቢያካሂድም የያዘውን ከማስቀጠል ውጪ የተለየ ለውጥ ማምጣት አልቻለም። በየአካባቢው የነበሩ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች የተደራጀ መልክ እየያዘ በተለይ በ2010 ዓ.ም ወደ ህዝባዊ አመጽነት ተቀይሯል። ይህንን አመጽ ለመቆጣጠር ለአስር ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ቢሆንም ተቃውሞው ይበልጥ እየበረታ በመሄዱ ለመቆጣጠር አዳጋች አድርጎታል። በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ ክልሎች እና በሌሎችም አካባቢዎች ተቃውሞው እየበረታ በመምጣቱ የጸጥታ ኃይሎች በሚወስዱት እርምጃ የሚሞቱ ሰዎች ከቀን ወደ ቀን እያሻቀበ ሊሄድ ችሏል።  በስተመጨረሻም በየካቲት ወር 2010 ዓ.ም የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው እንደለቀቁ በይፋ አሳውቀዋል።    

ይህን ተከትሎ የኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከመጋቢት 11 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለ17 ቀናት ያህል በዝግ ስብሰባ ከተወያየ በኋላ የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን የስልጣን መልቀቂያ ተቀብሎ በምትካቸው ዶ/ር ዐብይ አህመድ የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ። ይህን ተከትሎም ዶ/ር ዐብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ። አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቀሙት የህወሃት አባላት ዶ/ር ዐብይ በፓርቲ ሊቀመንበርነት በተመረጡበት ወቅት ጠንከር ያለ ተቃውሞ አቅርበው እንደነበርና በሚችሉት መንገድ ሁሉ ዶ/ር ዐብይ አህመድ እንዳይመረጡ ጥረት አድርገው እንደነበር በወቅቱ በስብሰባ ላይ የነበሩት ይገልጻሉ። ምንም እንኳን የህወሃት ቡድን አፈንጋጭነት አሁን ጎልቶ ይውጣ እንጂ ተቃርኖው የጀመረው በዚህ ወቅት ስለመሆኑ የብዙዎች እምነት ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ በአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መስኮች ዙሪያ ይስተዋሉ ለነበሩ ችግሮች መፍትሔ ሊሰጡ ይችላሉ ተብለው የታመነባቸው የለውጥ እርምጃዎች መውሰድ የጀመሩት እጅግ በፍጥነት ነበር። ከእነዚህ እርምጃዎች መካከል ለእስር ተዳርገው የነበሩ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች እና በርካታ ሰዎች በይቅርታና በምህረት እንዲፈቱ ተደርጓል። በውጭ አገራት በስደት ሲኖሩ የነበሩት ጥሪ ተደርጎላቸው ወደ አገራቸው እንዲገቡ ተደርጓል። ከጎረቤት አገራት በተለይ ደግሞ ከኤርትራ ጋር ሰላም እንዲፈጠር በመደረጉ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ሳይቀር አድናቆት የተሰጠው ተግባር ሆኖ አልፏል።

ከአገራዊ ለውጡ ዋነኛ ተጠቃሚ የሆኑት በአጋርነት ተፈርጀው የቆዩት የአርብቶ አደር አካባቢ ማህበረሰብ ናቸው። በለውጡ ማግስት የየክልሉ መሪዎች በአደባባይ ወጥተው “በክልላችን ራሳችንን በራሳችን እያስተዳደርን አልነበረም። ይልቁንም ህወሃት በእያንዳንዱ ክልልና ቢሮ ጭምር በአማካሪነት ስም በሚመድባቸው ጉልበተኛ የደህንነት ሰዎች አፈና ስር ነበርን” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ይህም ከለውጡ በፊት ህወሃት መራሹ መንግስት ምን ያህል የእጅ አዙር የሞግዚት አስተዳደር ስርዓት ዘርግቶ እንደነበር ማሳያ ነው።

ህወሃት ቀደም ሲል በተካሄዱ የድርጅቱ ጉባኤዎች ላይ በድርጅቱ ውስጥ የተፈጠሩ መበላሸቶች እንዲለወጡ እንዲሁም አንድ ትልቅና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገራዊ ፓርቲ የመመስረት ትልም እንደነበረው ሲናገር የቆየ ቢሆንም ከለውጡ በኋላ በተደረገው የፓርቲ ውህደትም ይሁን አጠቃላይ አገራዊ ለውጡን እንደማይቀበል መናገር የጀመረው ገና በጧቱ ነበር፡፡ የዚህ ውሳኔ ዋና ምክንያት ደግሞ ቀደም ሲል በሀገር ደረጃ በፖለቲካውና በኢኮኖሚው ላይ ይዞት የቆየውን የበላይነት ሊያሳጣው እንደሚችል በመገመቱ እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡

በአገራዊ ለውጡ የህወሃት ቡድን የፖሊስና የደህንነት መዋቅሩን ለሚፈልገው ዓላማ እንዲያመቸው የዘረጋውን አደረጃጀት ለማስተካከል በተወሰደው እርምጃ እና የብሔር ስብጥርን ባማከለ መልኩ በአዳዲስ አመራር የመተካት ስራ በመሰራቱ ህወሃት ደስተኛ አልነበረም። ይህን ተከትሎ በፌዴራል ደረጃ በከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ የነበሩ የህወሃት አመራሮችና በትስስሩ ውስጥ የነበሩት ሁሉ ወደ መቀሌ በመከተም አገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍና አገሪቱ እንዳትረጋጋ ስራዬ ብለው ተያያዙት።

የህወሃት ቡድን ጽንፈኝነቱ እያየለ ከመምጣቱም ባሻገር ከሌሎች ክልሎች ባፈነገጠ መልኩ ከፌዴራል መንግስት ጋር ለመስራት ያለመፈለጉን በተለያዩ ጊዜያት በወሰዳቸው እኩይ ተግባራት አሳይቷል። ከሌሎች ክልሎች የተለዩ ውሳኔዎችን ወስኗል፤ ፈጽሟል፤ አስፈጽሟል።

የብልጽግና ፓርቲ በሚመሰረትበት ወቅት ሁሉም የድርጅቱ አባላት እና አጋር ድርጅቶች ጭምር የአራቱን ፓርቲ ውህደት ሲደግፉት ህወሃት ብቻውን አፈንግጧል። ኢህአዴግ ወደ አንድ አገር አቀፍ ፓርቲነት የማሸጋገሩ ጉዳይ የረጅም ጊዜ ዕቅድ እንደነበርና የህወሃት አመራሮችም በተለያዩ መድረኮች ሲገልጹት የነበረ ቢሆንም ወደ ተግባር ሲገባ የህወሃት ጽንፈኞች እምቢተኝነታቸውን አሳይተዋል። ይህም “እኔ ያልመራሁት”  ከሚል የቆየ የህወሃት ቡድን ፍላጎት የመነጨ እንደሆነ ግልጽ ነው። ይህም ለጽንፈኛው ህወሃት የተቃርኖው ምእራፍ በጉልህ ያሳየ ነበር።

ጽንፈኛው የህወሃት ቡድን አገራዊ ፓርቲ በመመስረቱ የነበረውን የፈላጭ ቆራጭነት በትሩ እንደተነጠቀ በመገንዘቡ የሀሰት ፕሮፖጋንዳዎችን በተለያዩ አውታሮች አስተጋብቷል። የህወሃት ቡድን ሲያሰራጫቸው ከነበሩ የሀሰት ፕሮፖጋንዳዎች መካከል የብልጽግና ፓርቲ የተመሰረተው አገሪቱን ወደ አሃዳዊ አስተዳደር ለመቀየር ነው፣ አገሪቱን እያስተዳደር ያለው ፀረ-ፌዴራሊዝም አቋም የያዘ ነው፣ አገሪቱ ትበተናለች የሚሉና የተለያዩ የሀሰት ውንጀላዎችን ሲደሰኩር ቆይቷል።  በዚህ ፕሮፐጋንዳ ብቻ ሳይወሰን የፌዴሬሊስት ሃይሎች በሚል ካደራጃቸው ቡድኖች ጋር በመሆን በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሁከትና ብጥብጥ እንዲቀሰቀስ ያለእረፍት ሰርቷል። 

በአገራችን በተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት አገር አቀፍ ምርጫ ማካሄድ ባለመቻሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከህግ ምሁራንና የዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ብዙ ውይይትና ክርክር ካደረገ በኋላ የህገ መንግስት ትርጉም በመስጠት የተራዘመው ምርጫ ሁሉም ክልሎች ሲቀበሉት ህወሃት ግን ይህን ዴሞክራሲያዊ አካሄድ “ኢህገመንግስታዊና የስልጣን ጊዜ ለማራዘም የተደረገ ድራማ ነው” በማለት አጣጥሎታል።

ህወሃት የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔ ካለማክበሩም ባሻገር ህገ መንግስቱን በመጣስ በክልሉ የራሱን ምርጫ ኮሚሽን አቋቁሞ የምርጫ ቦርድ እውቅና ያልሰጠው ሕገ ወጥ ምርጫ አካሂዷል። ቡድኑ በዚህ ድርጊቱ በክልሉ ብቻውን ያሸነፈበትን ምርጫ ማካሄዱንም ተናገረ። የህወሃት ቡድን ህገ መንግስቱን በመጣስ ያካሄደው ምርጫ ተቀባይነት እንደማይኖረው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ሰጥቶበታል። በዚህ ውሳኔ የተበሳጨው የህወሃት ጽንፈኛ ቡድን “ግልጽ ጦርነት ታውጆብናል” ከማለቱም በላይ የፌዴራል መንግሰቱ ህገ ወጥና ማናቸውም መመሪያዎችና የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች እንደማይቀበል በይፋ አውጇል።  

የህወሃት ጽንፈኛ ቡድን በክልሉ የሚገኘውን የሰራዊት ሀይል ለውጊያ በሚያመች መልኩ ከማደራጀትም አልፎ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለጸጥታ ስጋት የሆኑ ጉዳዮችን ሲያከናውን ቆይቷል። የፌደራል መንግስቱ ሕገ ወጥ ነው ብሎ በይፋ በሚዲያ አሰራጭቷል። በትግራይ ክልል ያለውን የመከላከያ ሰራዊት እና ትጥቆችን ከቦታ ቦታ እንዳያንቀሳቅስ እንቅፋት ፈጥሯል። ይህም ብቻ አይደለም የሰሜን ዕዝን እንዲመሩ በፌዴራል መንግስት የተመደቡ ጀነራል መኮንን ከመቀሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እንዲመለሱ አድርጓል። በስተመጨረሻም ቀይ መስመር በማለፍ በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ በሌሊት ጦር አንስቶ ጥቃት ፈጽሟል፤ የጦር መሳሪያ ለመዝረፍም ሞክሯል።

መከላከያ ሃይላችን ሁላችን የምንኮራበት ታሪክ ያለው ለሃገራችን ሰላምና መረጋጋት መረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ከሃገራችን አልፎ ለተለያዩ ሃገሮችም ሰላማቸው እንዲሰፍን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገ ነው። በሃገራችን ህዝቦች ያለው ተቀባይነት ብቻ ሳይሆን ዓለምቀፋዊ ተቀባይነት ያለው ሃይልም ነው። በዚህ ሰራዊት ላይ ጥቃት መሰንዘር አገርን ለጠላት አሳልፎ ከመስጠት ያልተናነሰ የተወገዘ ተግባር ነው።

ህወሃት በመከላከያ ሰራዊት ላይ የሰነዘረው ጥቃት ሀገሪቱን ለመበተን ለበርካታ ዓመታት በግልጽም በድብቅም ሲሰራበት የነበረውን ዓላማ ለማሳካት ካለው ጽኑ ፍላጎት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ህወሃት ጦርነት ለመክፈት የበቃው አንድም ቀደም ሲል የነበረውን የፈላጭ ቆራጭነት ሚና ለማስመለስ አልያም ደግሞ ባለፉት ዓመታት ሀገሪቱን ሲያስተዳድር በነበረበት ወቅት ከላይ በተገለጹት ጉዳዮች ላይ ሲፈጽማቸው በነበሩ ወንጀሎችና ዘረፋ ተጠያቂ ላለመሆን በማሰብ ነው።

የፌዴራል መንግስት ከብዙ ትእግስት በኋላ በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃት የሀገር ሉአላዊነት መዳፈር ስለሆነ ህግ የማስከበር እርምጃ ለመውሰድ አስገድዶታል። ህግ የማስከበር ዘመቻው ብዙዎች እንደሚገምቱት በትግራይ ክልል በህገ-ወጥ መንገድ ምርጫ በመካሄዱ ምክንያት የተፈጠረ አይደለም። ህወሃት ውጊያውን የከፈተው በአገሪቱ እየተከናወነ ባለው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሪፎርም እምቢተኛ በመሆን ወደ ቀደመ የፈላጭ ቆራጭነት ቁመናው ለመመለስ ካለው ጥልቅ ፍላጎት የመነጨ ነው።

የህወሃት ጽንፈኛው ቡድን ለራሱ ስልጣን የሚጨነቅ ለህዝብ ቅንጣት ያህል የማያስብ ስግብግብ መሆኑን ከሚፈጽማቸው ተግባራት መገንዘብ ይቻላል። ህወሃት በስልጣን የመቆየት ህልሙ ሲነጠቅ “እኔ ያልመራሁት አገር ይፈርሳል” በማለት በይፋ አፍራሽ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል። አሁንም በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት የሰነዘረው በህዝብ ትግል ስልጣኑን እንዲያጣ የተደረገውን መልሶ ለመቆናጠጥ ነው። ልዩነቶችን በውይይትና በድርድር ከመፍታት ይልቅ ብቻውን ፈለጭ ቆራጭ የመሆን ምኞት የተላበሰ በመሆኑ ከሁለት ዓመታት በላይ በሩን ጥርቅም አድርጎ ዘግቶ በምሽግ ውስጥ አገሪቱን የማተረማመስ ተልእኮ ሲያከናውን ቆይቷል። ለሰላም የቀረበለትን ጥሪ እምቢ በማለት ህዝቡ ለጦርነት እንዲዘጋጅ አድርጓል። 

አሁን ለመላው ኢትዮጵያውያን ሁሉም ነገር ግልጽ ሆኗል። የህወሃት ጽንፈኛው ቡድን ምኞትም ከስሟል። ጽንፈኛው የህወሃት ቡድን ስልጣን ላይ ለመቆናጠጥ ያለውን ጥልቅ ፍላጎት ለማሳካት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት በመከላከያ ሰራዊታችን የሰሜን እዝ ላይ በፈጸመው ጥቃት ምክንያት መንግስት በወሰደው እርምጃ  በሶስት ምእራፎች ሲካሔድ በቆየው የህግ ማስከበር ዘመቻ የህሃት የጥፋት ቡድን ሊሸነፍ ችሏል፤ እውነት አሸንፏል። አሁን የሚቀረው ወንጀለኞችን አድኖ የመያዝና ወደ ህግ ማቅረብ ነው። ከዚህ በኋላ ወደ ልማታችን በመዞር የኢትዮጵያን ብልጽግና ማፋጠን ከሁላችንም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም