በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ዞን ከ48 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል

61
ሰቆጣ ሀምሌ 11/2010 በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በተያዘው የመኽር እርሻ ከ48 ሺህ 600 ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የሰብል ዘሮች መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡ የመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ደሳለኝ አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት በ2010/2011 የመኸር እርሻ በዘር ለመሸፈን ከታቀደው 120 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 48 ሺህ 651 ሄክታሩ በዘር ተሸፍኗል። እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴም ቀድሞ ዝናብ መጣል በጀመረባቸው አካባቢዎች ማሽላ፣ ገብስ፣ ስንዴና የባቄላ ሰብሎችን መዝራት መቻሉን ነው የገለጹት። በዝናብ መቆራረጥ ምክንያት አብዛኛው ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን እንዳልተቻለ የጠቆሙት አቶ ደሳለኝ፣ በቀጣይ መሬቱ ዘግይተው በሚለሙ የጤፍና የቅባት ሰብሎች እንደሚለማ ጠቁመዋል። በአካባቢው አልፎ አልፎ የሚጥለውን የዝናብ ውሃ በማጠራቀም ለመያዝ የሚያስችሉ የእርጥበት ማቆያ ስትራክቸሮች መሰራታቸውንም አመልክተዋል። እንደባለሙያው ገለጻ በተያዘው የመኽር ወቅት ከሚለማው መሬት ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል። "በመኽሩ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲቻልም 9ሺህ 800 ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል" ብለዋል። በሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ የቲያ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር በሩ አረቂ በበኩላቸው በሁለት ሄክታር መሳቸው ላይ ላለሙት የማሽላ፣ ገብስና ስንዴ ሰብሎች ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በአግባቡ መጠቀማቸውን ተናግረዋል፡፡ የግብርና ባለሙያን ምክረ ሃሳብ በመጠቀም በማሳቸው ዳር ውሃን ማቆር የሚችሉ አነስተኛ ጉድጓዶችን አስቀድመው ማዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል። በሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ የወለህ ቀበሌ አርሶ አደር ማሞ አስረስ በበኩላቸው ምርትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በወቅቱ አግኝተው ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ከግማሽ ሄክታር ለሚበልጠው የማሽላ ሰብላቸውም አንድ ኩንታል ማዳበሪያ መጠቀማቸውን የገለጹት አርሶአደሩ በእዚህም "ዘንድሮ የተሻለ ምርት እጠብቃለሁ" ብለዋል። በዞኑ ባለፈው የመኽር ወቅት ከ680 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት በአርሶ አደሮች መሰብሰቡ ይታወቃል ሲል የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም