በጁንታው ላይ የተወሰደው እርምጃ ለህግ የበላይነትና ለሃገር አንድነት መረጋገጥ ወሳኝ ነው….አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

103

ጋምቤላ፤ ህዳር 19/2013(ኢዜአ)የሃገር መከላከያ ሰራዊት በከሃዲው የህወሃት ጁንታ ላይ በወሰደው እርምጃ የተረጋገጠው የህግ የበላይነት ለዘላቂ ሃገራዊ አንድነትና ሰላም መረጋገጥ ትምህርት የሰጠ መሆኑን የጋምቤላ ክልል ርዕሰ-መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኦጁሉ ገለጹ። ርዕሰ መስተዳደሩ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የድሉን ብስራት ተከትሎ ርዕሰ-መስተዳደሩ ለኢዜአ እንደገለጹት የሃገር መከላከያ ሰራዊት በቡድኑ ላይ የወሰደውን ህግን የማስከበር እርምጃ በአጭር ጊዜ በድል በማጠናቀቁ የጋምቤላ ህዝብና መንግስት ታላቅ ደስታና ኩራት ተሰምቶታል።

ሰራዊቱ ለተራ የወንበዴ ስብስብ ቡድን መሸነፍ ይቅርና በጀግንነቱና በአይበገሬነቱ ለአፍሪካዊያን ሳይቀር ኩራት መሆኑን ተናግረዋል።

የህወሃት ጁንታ ቡድን በመላው ሃገሪቱ ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት የሴራ ፖለቲካን እያራመደ ሲዘርፍ የኖረ እንደመሆኑ እያንዳንዱ የቡድኑ አባል ተለቅሞ ተገቢውን ፍርድ ማግኘት እንዳለበት ገልጸዋል።

የድል ብስራቱ የመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ታላቅ የድል ቀን ሆኖ እውቅና የሚቸረው ዕለት እንደሆነም ርዕሰ-መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

በተደረገው ህግን የማስከበርና ሃገርን የማዳን ዘመቻ የጁንታው ቡድን መደምሰሱ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ዘላቂ ሃገራዊ አንድነትና ሰላምን ለማምጣት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑንም አቶ ኡሞድ አስረድተዋል።

በሃገራችን ከዚህ በኋላም ህወሃት የሚባል የጥፋት ቡድን የማንሰማበትን እድልን ላስገኘው የሃገር መከላከያ ሰራዊትና በትግሉ ለተሳተፉ አካላት በሙሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል።

“ከዚህ በኋላ የሚቀረው የጁንታውን ቡድን ከየቦታው አሰባስቦ ለህግ በማቅረብ ሁሉም ወደ ተጀመረው ልማት ፊቱን የሚያዞርበት ጊዜ ይሆናል” ብለዋል።

በተጨማሪም ሰላሙን አጥቶ የቆየውን የትግራይን ህዝብ በማረጋጋት ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር የማድረጉና የማገዙ ተግባር ሌላው የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ እንደሚሆንም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም