የስፖርት መሰረተ ልማቶች የጥራት ችግር የሚመነጨው ግንባታቸው በስፖርት ምህንድስና ባለሙያዎች ባለመከናወኑ ነው

84

አዲስ አበባ፣ ህዳር 19/2013(ኢዜአ) የስፖርት መሰረተ ልማቶች የጥራት ችግር የሚመነጨው ግንባታቸው በስፖርት ምህንድስና ባለሙያዎች ባለመከናወኑ ነው ተባለ።

የአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ስፖርት ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ ያካሄደ ሲሆን የ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና የ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት እቅድ ላይ መክሯል።

በጉባኤው በስፖርት ምክር ቤቱ አባላት ከተነሱት ሃሳቦች መካከል በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሚገነቡ የስፖርት መሰረተ ልማቶች ደረጃቸውን የጠበቁ አይደሉም፣ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ አይጠናቀቁም፣ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድም የላቸውም የሚሉ ናቸው።

የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽነር አማካሪ አቶ በሃይሉ በቀለ የስፖርት መሰረተ ልማቶች የጥራት ማነስ በክፍለ ከተሞች የተወሰነ ሳይሆን አገር አቀፍ ችግር መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

የችግሩ ምንጭ በኢትዮጵያ የሚገነቡ የስፖርት መሰረተ ልማቶች የሚገነቡት የስፖርት ምህንድስና እውቀት በሌላቸው ባለሙያዎች በመሆኑ ነው ብለዋል።

የስፖርት ምህንድስና የስፖርት መሳሪያዎችና መሰረተ ልማቶችን ንድፍ ማዘጋጀትና መስራትን አካቶ የያዘ የምህንድስና ዘርፍ ነው።

ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት የስፖርት መሰረተ ልማቶችን የሚገነቡት በስፖርት ምህንድስና ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ናቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የስፖርት መሰረተ ልማቶች የሚገነቡት ጥቅል የሲቪል ምህድስና እውቀት ባላቸውና የስፖርቱ እውቀት በሌላቸው ባለሙያዎች መሆኑ የጥራት ችግር እንዲፈጠር እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

በስታዲየሞች የሚገኙ የመሮጫ መም፣ መቀመጫዎች፣ የሜዳ ንጣፎችና ተያያዥ መሰረተ ልማቶች ላይ የጥራት ችግር የሚታየው የስፖርት ምሕንድስና እውቀት ባላቸው ሰዎች ባለመሰራቱ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአደይ አበባን ስታዲየም የሚገነቡት የቻይና መሐንዲሶች የስፖርት ምህንድስና ዘርፍ ባለሙያዎች በመሆናቸው ጥራቱን በጠበቀ መንገድ ግንባታው እየተከናወነ ነው ብለዋል።

'የችግሩን ምንጭ ካልፈታን አሁንም ወደፊትም በስፖርት መሰረተ ልማቶች ላይ የሚታየው ችግር መቀጠሉ አይቀርም' ያሉት አቶ በሃይሉ ችግሮችን ለመፍታት በዘርፉ የሰለጠነ ባለሙያ ማፍራት እንደሚሻና ለዚህም ሙያውን የተመለከተ ትምህርት ሊሰጥ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በጊዜያዊነት ለሲቪል ምህንድስና ባለሙያዎች የስፖርት ምህንድስና ስልጠና ሰጥቶ ወደ ግንባታ እንዲገቡ ቢደረግ መልካም እንደሆነም ጠቁመዋል።

በከተማ ደረጃ የስፖርት መሰረተ ልማቶችን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ በማያጠናቅቁ ተቋራጮች ላይ ውላቸውን የመሰረዝ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝም ነው አቶ በቀለ ያስረዱት።

የቅድመ ግንባታ ክፍያ ወስደው ወደ ስራ ያልገቡና የወሰዱትን ገንዘብ በስራ ላይ ያላዋሉ አንዳንድ ተቋራጮች ለሕግ እንዲቀርቡ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አክለዋል።

የባለቤትነት ሰነድ ማረጋገጫ የሌላቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ጉዳይ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር የተያያዘ መሆኑንም አመልክተዋል።

በማስተር ፕላኑ ያልተካተቱ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ እንደማያገኙና ለዚህም ችግር መፍትሔ የሚሰጠው ማስተር ፕላኑ እንደሆነ አክለዋል።

በአንዳንድ ክፍለ ከተሞች ለስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ የተሰጣቸውን ፈቃድ ለሌሎች የልማት ስራዎች የማዋል ሁኔታ እንደሚታይና ይህም ሊታረም የሚገባው ጉዳይ እንደሆነ ነው አቶ በሀይሉ የተናገሩት።

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ስፖርት ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ጠብቀው አመሸ በበኩላቸው በክፍለ ከተማው አስፈላጊውን መስፈርት ያሟላሉ የተባሉ የስፖርት መሰረተ ልማቶች 17 እንደሆኑና ከነዚህም ሶስት የእግር ኳስ ሜዳዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

በክፍለ ከተማው የሚሰሩ የስፖርት መሰረተ ልማቶች በተገቢው ጥራትና ጊዜ እንዲሰሩ ለማድረግ የቁጥጥርና የክትትል ስርዓቱን የማጠናከርና ሙያዊ ድጋፍ የመስጠት ተግባር እንደሚከናወን ገልጸዋል።

በ2013 ዓ.ም በክፍለ ከተማው የሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ቁጥር መጨመር፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ባህል ማዳበርና ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት ከዋነኛ ስራዎች መካከል ጠቅሰዋል።

በጉባኤው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የስፖርት ልማት ስራዎች አስተዋጽኦ ላደረጉ ተቋማትና ግለሰቦች የዋንጫና የምስክር ወረቀት ከዕለቱ የክብር እንግዶች ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም