የህወሃት ጁንታ በማይካድራ ማንነትን መሰረት አድርጎ በፈጸመው ጥቃት ላይ የሚደረገው ምርመራ ተጠናክሮ ቀጥሏል- ፌደራል ፖሊስ

63

አዲስ አበባ፣ ህዳር 19/2013(ኢዜአ) የህወሃት ጁንታ በማይካድራ ማንነትን መሰረት አድርጎ በፈጸመው ጥቃት ላይ የሚደረገው ምርመራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።

በማይካድራ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ልብ የሚሰብርና በሰው ልጅ ላይ የተፈጸመ የጭካኔ ተግባር መሆኑን በስፍራው የተገኙት የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ ተናግረዋል፡፡

ጥቃቱ በተለይ ሰላማዊ ሰዎችን ማዕከል በማድረግ መፈጸሙንም ነው የገለጹት፡፡

የተፈጸመው ጥቃት በእቅድና በፕሮጀከት እንደተመራ ጠቅሰው ሰዎችን ማፈናቀልና ለስራ የመጡ ሰላማዊ ሰዎችን በጭካኔ መጨፍጨፍ ልብን የሚሰብር ድርጊት ነው ብለዋል፡፡

የዚህ አይነት የግፍ ጭፍጨፋዎች በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች በህወሃት ቀጥተኛ ትዕዛዝ ሲፈጸም እንደነበር በተደጋጋሚ ስንገልጽ ቆይተናል ብለዋል ምክትል ኮሚሽነሩ፡፡

ማንኛውም ብሄር በኢትዮጵያ ውስጥ ተከባብሮ እንደሚኖርና በፈለገበት ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራት መብቱ የተጠበቀ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ከጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ጋር በመሆን የምርመራ ቡድን አዋቅሮ በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጭፍጨፋ ከተደረገበት ማግስት አንስቶ በአካባቢው ተሰማርቶ ስራውን እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ጥቃቱ የተፈጸመው የህወሃት ጁንታ ባሰማራቸው ሚሊሻዎችና ሳምሪ በሚባለው ቡድን መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በዚህም ንጹሃን ዜጎች በቤታቸውና በደጃቸው እንዲሁም በተገኙበት ቦታ በመዋቅር በተደገፈ መልኩ በክልሉ ፖሊስና ሚሊሻዎች በግፍ ተጨፍጭፈዋል ብለዋል፡፡

ለዚህም ያገኘናቸው ማስረጃዎች፣ ከጥቃት የተረፉ ሰዎች ፣የሟችና የተጎጂ ቤተሰቦች፣ በአካባቢው ለረጅም ጊዜ የኖሩ የትግራይ ተወላጆች የመሰከሩት ሃቅ ነው ብለዋል፡፡

ምርመራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው የተፈጸመውን ጥቃት ከኢትዮጵያዊያን ባለፈ አለም አቀፉ ማህበረሰቡ በሚገባ እንዲረዳው እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

ጥቃቱ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ካወጣው ሪፖርት በላይ እንደሆነና የተደረገው ድርጊት ከቁጥር በላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አሁን አስከሬኖች በተለያዩ ቦታዎች እየተገኙ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት በቤንሻንጉል፣ጉራፈርዳ፣ሶማሌ፣አማራ፣ ኦሮሚያ አካባቢዎች ለተፈጸሙት ግድያዎች ዋናው አንቀሳቃሽ መቀሌ የተደበቀው ቡድን እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ ወንጀለኞቹን ለህግ በማቅረብ የተጎጂ ቤተሰቦችንና የመላው ኢትዮጵያዊያንን እንባ በማበስ የህግ የበላይነትን እናረጋግጣለን ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም