"ንጹሃን ዜጎች ዒላማ ሳይሆኑ፣ ከተሞቻችንና ቅርሶቻችን ሳይጎዱ መቀሌ ለመግባት ተችሏል"- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

62

አዲስ አበባ፣ ህዳር 19/2013(ኢዜአ) ንጹሐን ዜጎች ዒላማ ሳይሆኑ፣ ከተሞቻችንና ቅርሶቻችን ሳይጎዱ የአገር መከላከያ ሠራዊት መቀሌ መግባቱን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጹ።

የትግራይ ሕዝብ ከስግብግቡ ጁንታ ጋር እንዳልሆነ በተግባር አስመስክሯልም ብለዋል።

ጁንታው ካስታጠቃቸው ጥቂት የክፋት ኃይሎች ውጭ ያለው የትግራይ ሕዝብ መቀሌ እስኪገባ ድረስ ለመከላከያ ሠራዊቱ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ሁሉ አድርጓል።

የመከላከያ ሠራዊት በድል በገሠገሠባቸው የትግራይ አካባቢዎች ሁሉ የትግራይ ሕዝብ ለሀገሩ ያለውን ፍቅርና ለመከላከያ ሠራዊቱ ያለውን ክብር አሳይቷል።

ይህም የሠራዊቱን ድልና የጁንታውን ሽንፈት አፋጥኖታል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ።

ስግብግቡ ጁንታ በየትኛውም መመዘኛ ለትግራይ ሕዝብ አይመጥነውም፤ የትግራይ ሕዝብ ከእውነት ጋር በመቆምና የጁንታውን እኩይ ዓላማ በመፃረር ከቀበሌ ቀበሌ፣ ከዞን ዞን መቀሌ እስኪገባ ድረስ ተመሳሳይ ድጋፍ ለሠራዊቱ ሰጥቷል፤ "ለዚህም ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ" ብለዋል።

ጁንታው በሸሸበት ከተማና አካባቢ ሁሉ የጤና ተቋማትን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ድልድዮችን፣ መንገዶችን፣ መሥሪያ ቤቶችን እያወደመ ሄዷል፤ በዚህም የገዛ ወገኑ ጠላት መሆኑን አሳይቷል።

ጁንታው እኔ ከሞትኩ ብሎ ያፈረሳቸውን መሠረተ ልማቶች በፍጥነት በመገንባት የትግራይ ሕዝብ ወደ ሠላማዊ ኑሮው እንዲመለስ ለማድረግ የቻልነውን ሁሉ እንደምናደርግ ቃል እገባለሁ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም