በጀቱ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል በመቆጣጠር ለውጡን እንደሚያስቀጥሉ የአማራ ክልል የምክር ቤት አባላት ገለጹ

97
ባህርዳር  ሀምሌ 11//2010 የመንግስት በጀት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል አስፈጻሚውን አካል በሚገባ በመቆጣጠር ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል የድርሻቸውን እንደሚወጡ  የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡ የክልሉ ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ባካሄደው አስረኛ መደበኛ ጉባኤ ከ43 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አጽድቋል። ይህንን ተከትሎ የኢዜአ ሪፖርተር ካነጋገራቸው የምክር ቤቱ አባላት መካከል ወይዘሮ የሺወርቅ ጌታሁን እንዳሉት የህብረተሰቡን ቅሬታዎች ለመፍታት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተመደበላቸውን በጀት ለታለመለት ዓላማ በወቅቱ  እንዲያውሉ ትኩረት ይደረጋል። የአስፈጻሚ አካላትን ሪፖርት ማዳመጥ ብቻ ሳይሆን በተግባር ያከናወኗቸው ስራዎችና የተገኙ ውጤቶች እንደሚገመግሙ ተናግረዋል። ይህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተጀመሩ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ማሳደግና ህዝባዊ አንድነት ለማስቀጥል የሚያግዝ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከአስፈጻሚው አካል ጋር ስራን ቆጥሮ የመረከብና የማስረከብ አካሄድን ለመከተል መዘጋጀታቸውን የምክር ቤቱ አባል አስታውቀዋል፡፡ የአስፈጻሚ አካላት እቅዶች የት ደረሱ፣እንዴት ተሰሩ የሚሉ የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች ምክር ቤቱ በበጀት ዓመቱ ከዚህ ቀደም በተለየ መልኩ ለመስራት እንደወሰነ የተናገሩት ደግሞ አቶ ብሩ ይማም ናቸው። እርሳቸው እንዳመለከቱት የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ለማስቀጠልና የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ ዋናው ተግባር  አስፈጻሚ አካላትን መቆጣጠር ነው። አቶ ወርቁ ኃይለማሪያም የተባሉት ሌላው የምክር ቤቱ አባል  በበኩላቸው አሁን በክልሉ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር በመፍታት  ከድህነት ለመላቀቅ እንዲያግዝ የተመደበውን በጀት በአግባቡ መጠቀም ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል። አቶ ወርቁ ይህንን ለማከናወን በየደረጃው ያሉ የምክር ቤት አባላት ዝግጁ እንደሆኑ ገልጸዋል። በክልሉ ለ2011 የስራ ዘመን የተመደበው በጀት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ15 በመቶ ብልጫ እንዳለው  ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም