ወደ አስመራ ያቀናው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ስኬታማ ነበር-ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

81
አዲስ አበባ ሐምሌ 11/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ20 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ወደ ኤርትራ ርእሰ መዲና አስመራ ያደረገው መደበኛ በረራ የተሳካ እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ አውሮፕላኑ ዛሬ ጠዋት ወደ አስመራ የተጓዘው የቀድሞው የኢፌደሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ 465 መንገደኞችን አሳፍሮ ነው። የመንገደኞቹ ልዑካን ባለሃብቶችን፣ የኪነ-ጥበበ ሙያተኞችን፣ ጋዜጠኞችን እና ለዓመታት ከቤተሰቦቻቸው ተለያይተው ኢትዮጵያ ይኖሩ የነበሩ  ኤርትራውያንን ያካተተ ነው። የልዑካን ቡድኑ አስመራ ሲገባ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳላህና የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አምባሳደር ዘመደ ተክሌን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሀገሪቱ ባለስልጣናት አቀባበል አድርገውለታል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዛሬ ጀምሮ በየሳምንት ሁለት ጊዜ ወደ አስመራ እንደሚበርም ተገልጿል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም