በገንዳውሃ በህገ-ወጥ የቤንዚል ንግድ ምክንያት ስራችንን በአግባቡ ማከናወን አልቻልንም - የባጃጅ አሽከርካሪዎች

74
መተማ ሀምሌ 11/2010 በህገ-ወጥ የቤንዚን ንግድ ምከንያት ለህብረተሰቡ ተገቢውን የመጓጓዣ አገልግሎት ለመስጠት መቸገራቸውን በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳውኃ ከተማ ባጃጅ አሽከርካሪዎች ተናገሩ፡፡ በከተማው ባጃጅ በማሽከርከር የሚተዳደረው ወጣት መካሻው ሙላት ለኢዜአ እንዳለው በህገ-ወጥ ንግድ ምክንያት በከተማው የቤንዚን እጥረት ተከስቷል። ራሱንና ቤተሰቡቹን በዚሁ ስራ ያስተዳድር እንደነበር ወጣቱ ጠቁሞ በቤንዚን እጥረት ስራው መስተጓጎሉን ተናግሯል። ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት አየለ ግርማ በበኩሉ ”ቤንዚል ከማደያዎች ስንጠይቅ የለም የምንባልበት ምክንያት በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሌላ አካባቢ ስለሚሄድ ነው” ሲል ተናግሯል፡፡ ”የአንድ ሊትር ቤንዚን 19 ብር ቢሆንም ከቸርቻሪ ግለሰቦች እስከ 40 ብር ድረስ እየገዛን ስለምንሰራ ውጤታማ ሊያደርገን አልቻለም›› በማለት አስረድቷል፡፡ ሌላው አስተያየት ሰጪ ወጣት አስቻለው ጋሸ በበኩሉ ''ለቤንዚን ግዢ የምናወጣው ወጪ ከባጃጅ ትራንስፖርት ታሪፍ ጋር ስለማይጣጣም ለኪሰራ እየዳረገ ነው'' ብሏል፡፡ የምዕራብ ጎንደር ዞን ንግድና ኢንዱስትሪ ገበያ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ክብረት ሙጨ በአካባቢው የሚታየውን ህገ-ወጥ የቤንዚል ንግድ ለመከላከል ሁሉም ወረዳና ከተማ አስተዳደሮች እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቅርቡ በህገ-ወጥ ገበያ ሲሸጥ የነበረ ከ500 ሊትር በላይ ቤንዚን መያዙን ጠቅሰው ከገንዳውሃ ማደያዎች በህገ-ወጥ መንገድ የሚወጣበትን መንገድ ለመቆጣጠር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የገንዳውኃ ንግድና ኢንዱስትሪ ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ አዱኛ አዲሱ ህጋዊ ፈቃድ ያላቸው ቸርቻሪዎች ብቻ ቤንዚን እንዲሰጣቸው በከተማው ከሚገኙ ማደያዎች ጋር ከስምምነት መደረሱን አስታውቀዋል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከጉምሩክ ጋር በቅንጅት እንደሚስራ ሃላፊዋ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም