የኢትዮጵያ ፕሮፌሰሮች ካውንስል ተመሰረተ

87

አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2013(ኢዜአ) በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ባለሙሉ ፕሮፌሰሮች ካውንስል ተመሰረተ።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በበይነ መረብ በመታገዝ የካውንስሉን የምስረታ ጉባዔ አካሂዷል።

የካውንስሉ ምስረታ ምሁራን ከሚኒስቴሩ ጋር በመቀናጀት የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ግቦችን ለማሳካትና በአገር ልማት አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትን መንገድ ለመፍጠር ያለመ ነው።

ምሁራኑ ለአገራቸው ብልጽግና በዕውቀታቸው አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ካውንስሉ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ ይደራጃል ተብሏል።

ካውንስሉ የመምህራንና የአሰልጣኞች ልማት፣ የትምህርትና ስልጠና ጥራትና አግባብነት፣ የምርምር ጥራት አግባብነትና ተደራሽነትን ጨምሮ ሰባት የትኩረት መስኮች እንዳሉትም ተገልጻል።

በተጨማሪም የአካዳሚክ፣ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የዓለም አቀፍ ሃብት ማፈላለግ ጉዳዮችን የሚያካትቱ አምስት ቋሚ ኮሚቴዎችን አደራጅቶ ሥራውን ይከውናል ነው የተባለው።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ዑርቃቶ ካውንስሉ የተቋቋመው ኢትዮጵያዊያን ምሁራን ለአገራቸው ልማት የዕውቀት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ መሆኑን ገልፀዋል።

ምሁራኑ በአገር በቀል የምጣኔ ሃብት ማሻሻያው ትኩረት በተደረገባቸው ማዕድን፣ ግብርና፣ ቱሪዝምና ሌሎችም ዘርፎች ሙያዊ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው የካውንስሉን የትኩረት መስኮችና አደረጃጀት ባቀረቡበት ጽሁፍ ምሁራኑ በመምህራንና አሰልጣኞች ልማት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ካውንስሉ የበላይ ጠባቂ የሚኖረው ሲሆን ተጠሪነቱ ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ይሆናል።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰሩ፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚያገለግሉ፣ በምርምር ተቋማት የሚሰሩና በጡረታ ላይ ያሉ ባለሙሉ ፕሮፌሰሮች በፈቃደኝነት የካውንስሉ አባል መሆን ይችላሉም ተብሏል።

በጉባዔው ከ170 በላይ ባለሙሉ ፕሮፌሰሮች ከአገር ውስጥና ከውጭ አገራት በበይነ መረብ አማካኝነት ተሳትፈዋል።

ከተሳታፊዎቹ አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ካውንስሉ ባላቸው ዕውቀት አገራቸውን ማገልገል እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጤና፣ በግብርናና ሌሎች ዘርፎች የሚሰሩ 236 ባለሙሉ ፕሮፌሰሮች እንዳሏት ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም