የኦሮሚያ ልማት ማህበር በሰሜን ሸዋ ዞን በ21 ሚሊዮን ብር የልማት ሥራዎች እያካሄደ ነው

73

ፍቼ ኀዳር 18/2013 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ልማት ማህበር በሰሜን ሸዋ ዞን አምስት ወረዳዎች ከ21 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተለያዩ የልማት ሥራዎች እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ።

የማህበሩን ገቢ ማጎልበት በሚቻልበት  ዙሪያ   ከዞኑ 13 ወረዳዎች  ከተወጣጡ የማህበሩ አስተባባሪዎችና ተወካዮች ጋር ዛሬ በፍቼ ከተማ ውይይት ተካሄዳል።

የልማት ማህበሩ የሰሜን ሸዋ ዞን ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ዋቅጅራ በውይይት መድረኩ እንዳሉት  ማህበሩ እያካሄዳቸው ያሉት የልማት ሥራዎች ዘንድሮ የተጀመሩና  እስከ መስከረም ወር 2014 ዓ.ም ድረስ ለማጠናቀቅ የታቀዱ ናቸው።

ለማስፈጸሚያውም  21 ሚሊዮን 500ሺህ ብር መመደቡን አስታውቀዋል።

የልማት ስራዎች የሚካሄዱት በወረዳዎቹ በመንገድ ችግር ለትራንስፖርት አገልግሎት አዳጋች በሆኑ ቆላማ ቀበሌዎችና ሸለቆማ ስፍራዎች መሆኑን አስረድተዋል። 

ከልማት ስራዎቹ መካከል ሁለት የጤና ኬላዎች፤ 12 መካከለኛ የውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮና 27 ምንጭ ማጐልበት እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል።

ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁም  ከ25ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ብለዋል። 

ለዚህም የአካባቢው ሕብረተሰብም ከጉልበቱ በተጨማሪ ከአምስት መቶ ሺህ ብር በላይ አዋጥቶ እየተሳተፈ መሆኑን  ጠቁመዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ የውይይቱ ዓላማ የማህበሩ አባላትና ደጋፊዎች የሚያደርጉትን ሁለገብ ድጋፍ  አጠናክረው እንዲቀጥሉ ከማነሳሳት በተጨማሪ አዳዲስ የገቢ ማስገኛ ኘሮግራሞችን በማዘጋጀት ገቢው እንዲጎለብት ለማነሳሳት ነው።

የማህበሩ የሂደቡ አቦቴ ወረዳ ተወካይ አቶ ሙዘይን ፋሪስ ማህበሩ የህብረተሰቡን ልማት ጥያቄ ለመመለስ መንግስት የሚያደርገውን እንቅስቀሴ በመደገፍ በግልጽና ጠያቂነት መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል። 

ለሚያከናውናቸው ሥራዎችም በአባልነት ያቀፋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ አስተባባሪዎች በትጋት መስራት አለበን ብለዋል።

ሌላው የማህበሩ የፍቼ ከተማ አስተባባሪ አቶ ቃሲም አሊ በበኩላቸው ማህበሩ በልማት ወደኋላ ለዘገዩ አካባቢዎች ቅድሚያ በመስጠት የሚያከናውናቸው ሥራዎች የሚበረታታ መሆኑን  ተናግረዋል። 

በማህበሩ ውስጠ የሚታዩ ጉድለቶችን ለይቶ ለማስተካከል ውይይቱ መዘጋጀቱ መልካም መሆኑን ገልጸዋል።

ማህበሩ ባለፉት ሁለት ዓመታት በዞኑ ሰባት ወረዳዎች ከአባላትና ደጋፊዎች  መዋጮ  በተሰበሰበ 10 ሚሊዮን 800ሺህ ብር  ወጪ ከሃያ ሺህ የሚበልጡ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ስራዎች እንደተከናወኑ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም