እኔ ከሞትኩ…

93

በጥላሁን አያሌው ( ኢዜአ)

ኢትዮጵያ በታሪክ ስትወሳ የአክሱም የሥልጣኔ ዘመን መሣ ለመሣ መነሳቱ አይቀሬ ነው። የአክሱም ዘመንን ከፍታ ከሚያጎሉ ነገሮች ደግሞ የአክሱም ኃውልት አንዱ ነው። የኢትዮጵያውያን የጥበብ አሻራ ማህተም፣ የሀገራችን ታሪክ ዘካሪ እንዲሁም ሀገሪቷ ከሚትታወቅበት ቅርስ  ተጠቃሽ የሆነው የአክሱም ኃውልትም በርካታ ሚስጥራትን የያዘ ዓለምአቀፍ ሀብት ጭምር ነው። ይህንን የታሪክ አናት የሀገር አምድ ለመጎብኘትም ከአራቱም የዓለም ማዕዘናት ጎብኚዎች ወደሀገራችን ይተማሉ።

ከዚህም በተጨማሪ አክሱም የሙሴ ጽላት እንደሚገኝባት የሚታመነው የአክሱም ጽዮን ማርያም ቤተክርስቲያን መገኛም ነች። የውጭ ሀገር ሰዎች በቤተክርስቲያኗ እንዳለ በሚታመነው ጽላተ ሙሴ፣ ኢትዮጵያውያን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ደግሞ በየዓመቱ ህዳር 21 የሚከበረውን የጽዮን ማሪያም በዓልን ለማክበር በአየርና በየብስ ወደአክሱም ይተማሉ። ስለሆነም የአክሱም ከተማ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የታሪክ፣ የቅርስና የማንነት መገለጫ ብቻ ሣይሆን ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ጭምር ናት።

አክሱም በአየርና በየብስ የሚጎበኟትን እንግዶች ከምትቀበልባቸው መንገዶች መካከል አንዱ የአክሱም አየር ማረፊያ ነው። ይህ የአየር ማረፊያ ከተማዋ የሚጎበኟትን እንግዶች ፍሰት ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተሰራ ሲሆን፤ በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ካሉና በርካታ በረራ ከሚያስተናግዱ አየር ማረፊያዎች መካከል አንዱ ነው። ለአካባቢው ማህበረሰብም የሥራ ዕድልና የገቢ ምንጭ መፍጠር የቻለ ነው።

ከሰሞኑ በህወሃት ውስጥ የመሸገው ህገ ወጥ ቡድን በመከላከያ ሰራዊታችን እየደረሰበት ያለውን ሽንፈት ተከትሎ በክልሉ የሚገኙ ትልልቅ መሰረተ ልማቶች ላይ ውድመትን እያስከተለ ይገኛል። ሆን ተብለው እንዲወድሙ ከተደረጉት መሠረተልማቶች መካከል የአክሱም አየር ማረፊያ አንዱ ነው።

መሰረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰው ውድመት እንደ ኢትዮጵያ ገና በማደግ ላይ ባሉ አገራት ላይ የሚያሳድረው ኢኮኖሚያዊ ጫናው ከባድ ነው። የኮንስትራክሽን ዘርፍ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት በመሰረተ ልማት ላይ የሚደርስ ጉዳት አንድን አገር እጅግ ወደኋላ የሚያስቀር ነው። በአክሱም ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ላይ የደረሰው ጉዳትም እንደአገርና እንደ ህዝብ ኪሳራው ከፍተኛ ነው።

የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማናጅመንት ኢኒስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶ/ር አርጋው አሻ ከፋና ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ የአክሱም አየር ማረፊያ የሚሰጠው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎት ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል። ከተሳፋሪዎች ምልልስ አንፃር በጣም ታዋቂና የተጨናነቀ አየር ማረፊያ መሆኑንም አያይዘው ተናግረዋል። ይህ አየር ማረፊያ ከአዲስ አበባ በሳምንት 28 በረራዎች፣ ከመቀሌ አራት በረራዎች እንዲሁም ከጎንደር ሁለት በረራዎች በድምሩ ወደ 34 በረራዎችን በሳምንት እንደሚያስተናግድ ዶ/ር አርጋው አመልክተዋል።  

ይህ ዓለም አቀፍ የአየር ማረፊያ ለአካባቢው ማህበረሰብ የሥራ ዕድል ያስገኘ፤ የመኖር ህልውናቸው ከኤርፖርቱ ጋር የተገናኘም በርካቶች ናቸው። የአክሱምን ሃውልት ጨምሮ የተለያዩ የቱሪስት መስህቦችን ለመጎብኘት ወደ ስፍራው በርካታ ቱሪስቶች የሚፈሱ እንደመሆኑ መጠን የአካባቢው ነዋሪዎች የእለት ተእለት ኑሮዋቸው ከአየር ማረፊያው ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት አለው። በመሆኑም በአየር ማረፊያው ላይ የደረሰው ውድመት የበርካታ የአክሱም ከተማና አካባቢው ማህበረሰብ የዕለት ጉርሱ እንዲቋረጥ አድርጓል። በተለይም በየዓመቱ ህዳር 21 በድምቀት የሚከበረው የፅዮን ማርያም ክብረበዓል ለማክበር ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት በጥፋት ቡድኑ የደረሰው ውድመት ለህዝቡ ምንም እንደማይጨነቅ ግልጽ ማሳያ ነው።

የአክሱም ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከ526 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት ይነገራል። አንድ አየር ማረፊያ ለመገንባት በተለይ አውሮፕላኑ የሚንደረደርበትና የሚያርፍበት ቦታ በካሬ ሜትር ከአራት እስከ አምስት ሺህ ብር እንደሚፈጅ ዶ/ር አርጋው ይናገራሉ። በዚህ ስሌት አሁን ባለው ዋጋ ለኤርፖርት ግንባታ ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ ይጠቅሳሉ። የአክሱም አየር ማረፊያን  መንደርደርያና ማረፊያ ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰበት እሱን መልሶ ለመገንባት እንደአዲስ መስራትን እንደሚጠይቅ ይናገራሉ። ይህንን ለማድረግ ራሱን የቻለ ጥናት እንደሚጠይቅና ግብዓቶችንም ከውጭ ማስመጣትና ደረጃውን ጠብቆ እንዲሰራ ማድረግ ጊዜ እንደሚወስድ ይገልጻሉ። 

የህወሃት የጥፋት ቡድን የአክሱምን አየር ማረፊያ ብቻ ሳይሆን ወደ መቀሌ የሚወስዱ ድልድዮችን በማፍረስና የአስፋልት መንገዶችንም በመቆፋፈር ከጥቅም ውጪ አድርጓል። አሁን ባለው የገበያ ዋጋ ሰባት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው አንድ የአስፋልት መንገድ ለመስራት እስከ 30 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ በመግለጽ ውድመቱ ከባድ ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ እንደሚያሳርፍ ዶ/ር አርጋው ይገልጻሉ። በትግራይ ክልል በመንገዶች ላይ የደረሰው ውድመት ወደ ገንዘብ ቢሰላ 30 ጤና ጣቢያ ሊያሰራ እንደሚችልም አያይዘው ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል የሚገኝ ማንኛውም መሰረተ ልማት ለአካባቢው ነዋሪ የጋራ ሃብቱ ነው። እያንዳንዱ መሰረተ ልማት ከህይወቱ ጋር የተቆራኘ ነው። መንገድ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚያገናኝ እንደመሆኑ መጠን የንግድ ልውውጥ ለማድረግም ይሁን ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮችን ለማከናወን የሚያስችል ነው። እናም የህወሃት ጽንፈኛ ቡድን “እኔ ካልኖርኩ…” በሚል ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያን የመሰለ መሰረተ ልማት አፈራርሷል። ህዝቡ የሚገለገልበትን መንገድ ቆፋፍሯል።

አክሱምን የመሰለ ታሪካዊ ቦታ ላይ ጥቃት ያደረሰው የህወሃት የጥፋት ቡድን ለሩብ ምዕተዓመት ኢትዮጵን በበላይነት እንዳሻው ሲያሾራት የቆየ አካል ነው። በዚህ ድርጊቱ ለትግራይ ህዝብ ጥቅምና መብት ቆሜያለሁ ሲል የኖረው የህወሃት አጥፊ ቡድን ደንታ ቢስነቱንና ዘራፊነቱን በግልጽ አሳይቷል።

ህወሃት በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመውን ያልታሰበና ነውረኛ ጥቃትን ተከትሎ የፌዴራል መንግስት እያካሄደው ያለውን ህግን የማስከበር ዘመቻ መቋቋም ተስኖት በማፈግፈግ ላይ ሲሆን ትቷቸው በሸሸባቸው ከተሞችም ጥፋትና ውድመት እያደረሰ ይገኛል። ከዚህ ቀደም ሲያደርገው እንደነበረው ህግ የማስከበር ዘመቻው ከተጀመረ በኋላም ራሱን ለባሰ ተጠያቂነት የሚያበቁ ታሪካዊ ስህቶችን ከመፈጸም አልተቆጠበም። በጥፋት ላይ ጥፋት፤ በወንጀል ላይ ሌላ ወንጀል እየፈጸመ ነውረኝነቱን ቀጥሎበታል።

እየፈጸማቸው በሚገኘው እኩይ ተግባራቱ እውነተኛ ማንነቱን ያሳዩና ስለልማት፣ ሠላምና ዴሞክራሲ ሲያደርግ የነበረው ስብከት የይስሙላ እንደነበር እየተጋለጠ መሆኑን ብዙኃኑ መታዘብ ችለዋል። በማይካድራ ከተማ ከ600 የሚልቁ ምንም የማያውቁና ጉዳዩ የማይመለከታቸው ንጹኃን ዜጎች መጨፍጨፉን የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ኮሚሽን በመጀመሪያ ዙር ሪፖርቱ አሳውቋል። ቡድኑ የፍልሚያ ቀጠና ወዳልሆኑት ባህር ዳርና ጎንደር ተደጋጋሚ ሮኬቶችን በመተኮስ በንጹሀን ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ለማድረስ ሞክሯል።  

ይህ ስግብግብ ቡድን በትግራይ ህዝብና በኢትዮጵያውያን የተገነቡ በርካታ መሠረተ ልማቶችን አውድሟል። ‘እኔ ከሞትኩ…’ በሚል የራስ ወዳድነት ብሂል ድልድዮችን ሰባብሯል። ለትግራይ ህዝብና ለኢትዮጵያ ትልቅ ትርጉም ያለው የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያን እንዳልነበረ አድርጎታል። ይህ ተግባሩም ጥፋት ተፈጥሯዊ ባህሪው መሆኑንም በግልጽ አሳይቷል። በትግራይ ህዝብ ስም ሲምልና ሲገዘት የኖረው ህወሃት የትግራዋይን ሀብትና ንብረት በማውደምም አስመሳይነቱን ለዓለም አጋልጧል። መሠረተ ልማት ለትግራይ ክልልና ለትግራይ ህዝብ ምን ማለት እንደሆነ እየታወቀ የጥፋት ቡድኑ ግን በደንታ ቢስነት ህዝቡ እንዳይጠቀም ልማቱን ማውደም ተያይዞታል። ስብስቡ በፈጸመው ነውረኛ ተግባርም ስለራሱ ጥቅምና ምቾት ብቻ የሚጨነቅ እንጂ ለህዝብ ልማትና ተጠቃሚነት የማያስብ መሆኑን ያስመሰከረበት ታሪክ የማይረሳው ጥፋት እየፈጸመ ይገኛል።ሠላም!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም