ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከአፍሪካ ህብረት ልኡካን ጋር ተወያዩ

58

ህዳር 18/2013 (ኢዜአ) መንግሥት ከሁለት ዓመት በላይ የህወሃትን የጥፋት አካሄድ በመታገስ ሰላማዊ ጥሪ ሲያደርግ ቢቆይም ሕወሃት ግን ይህን ባለመቀበሉ የህግ ማስከበር ዘመቻው እየተካሄደ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አህመድ ዛሬ የአፍሪካ ሕብረት ልዑክ ተቀብለው አነጋግረዋል።

የአፍሪካ ሕብረት የላከው ልዑክ ሶስት የቀድሞ መሪዎችን በአባልነት የያዘ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጽህፈት ቤታቸው በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያነጋገሩት የቀድሞ የላይቤሪ ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንስን ሰርሊፍ ፣ የሞዛምቢክ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጆአኪም ቺሳኖንና የደቡብ አፍሪካን የቀድሞ መሪ ካግሊማ ሞታህነቴ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚህ ወቅት ልዑኩን የላኩት የህብረቱ ሊቀመንበር ሲሪል ራማፎሳ መንግሥት እየወሰደ ያለውን የህግ ማስከበር ዘመቻና የሕወሃት ቡድንን ለፍትህ ለማቅረብ እየተካሄደ ያለውን ተግባር በመረዳታቸው ምስጋና አቅርበዋል።

በተጨማሪም የልዩ ልዑኩ አባላት የቀደመ ወዳጅነትን በመረዳት ለኢትዮጵያ ያለውን አክብሮት ማሳየቱ ለቀጣይ የወንድማማችነትና የብልጽግና ጉዞ ያሳየውን መረዳት አድንቀዋል።

“ይህም የአፍሪካን ጉዳዮችን በአፍሪካውያን መፍትሄ እንዴት መመለስ እንደሚያስችል ማሳያ ነው” ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም መንግሥት በትግራይ እያካሄደ ያለውን የህግ ማስከበር ዘመቻ ሂደት አስገንዝበዋል።

መንግስት ከሁለት ዓመት በላይ የህወሃትን የጥፋት አካሄድ በመታገስ ሰላማዊ ጥሪ ሲያድርግ እንደነበር አስታውሰዋል።

“በህወሃት ቡድን የሚደረጉ ትንኮሳዎችን በመታገስም መንግስት የሰላም በሩን ከፍቶ እንደነበርና በመከላከያ ሰራዊት ላይ የተቃጣው ጥቃት ግን አገራዊ ህልውናን የሚያናጋ በመሆኑ የህግ ማስከበር ዘመቻው በመካሄድ ላይ ነው” ብለዋል።

መንግስትም በህገመንግስቱ በተጣለበት ሃላፊነት አገርን የማስቀጠል ተልእኮውን እየተወጣ እንደሚገኝ ነው ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም