ህወሃት መሰረተ ልማት ማውደሙ ለትግራይ ህዝብ እንደማያስብ ያረጋገጠ መሆኑን የትግራይ ተወላጆች ገለጹ

55

ደሴ፣ ህዳር 18/2013( ኢዜአ) ህወሓት በከፍተኛ ወጭ የተሰሩ መሰረተ ልማቶችን ማውደሙ ለትግራይ ህዝብ እንደማያስብ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን በደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ገለፁ፡፡ 

ከተወላጆቹ መካከል  አቶ ገብረመድን መብራቱ ለኢዜአ በሰጡት አሰተያየት ህወሓት ከምስረታው ጀምሮ ድብቅ የጥፋት ተልዕኮ ያለው ሀገር አፍራሽ  ሆኖ የተቋቋመ ቡድን ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የምትባል ሉዓላዊት ሀገር እንዳትኖር የረጅም ጊዜ እቅድ ይዞ ከውጭ ጠላት ጋር ጭምር ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመው "ተግባሩን የሚቃወሙትን አስሮ  ገርፏል፣ ረሽኗል፣ አሳዷል፣ አካል ጉዳተኛም አድርጓል" ሲሉም ገልጸዋል፡፡

"እኔም የህወሃትን ሃሳብ ባለመደገፌ  ከአምስት ወንድሞቼ ጋር ክልሉን እንድለቅ ተገድጃለሁ ያሉት አቶ ገብረመድን በዚህም ምክንያት  አቅመ ደካማ እናታቸውን ትተው በመበታተን ተነፋፍቀው እንደሚኖሩ  ተናግረዋል።

ቡድኑ በቀለኛ በመሆኑ ክልሉን ለቀው ሲወጡ የነበራቸውን  የአትክልት ልማት ቦታ ቀምቶ ለደጋፊዎቹ በመስጠት እናታቸው ለችግር እንዲጋለጡ ማድረጉን ገልጸዋል።

አሁን ላይ የትግራይ ህዝብ እንደሚደግፈው በማስመሰል እየተወሰደበት ያለውን እርምጃ በህዝብ ላይ የተከፈተ ጦርነት ነው ማለቱ ቅዠት እንጂ ከእውነት የራቀ ነው ብለዋል።

የተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ መንግስትም ነጻ የወጡ አካባቢዎች ላይ መዋቅሩን በመዘርጋት ህዝቡን የማረጋጋትና የልማት ስራዎች እንዲያከናውን የሚደግፉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የመሰረተ ልማቶችን መልሶ በማቋቋም  ህዝቡ  ወደ እለት ተዕለት ኑሮው እንዲመለስ አስፈላጊው ድጋፍ ሊመቻችላቸው እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ሌላው ተወላጅ  አቶ መንግስቱ ፀጋዬ በበኩላቸው  የትግራይ ህዝብ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በመፈቃቀር የሚኖር ነው ብለዋል።

ሆኖም የህወሓት ቡድን በስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት  ከእህት ወንድሞቻቸው ለመለየት ተንኮል ሲሸርብ መኖሩን አውስተዋል።

በትግራይ ክልል ህዝብ ላይ ሲፈፅም የኖረው አፈና፣ ጭቆና፣ ማሳደድና ሌሎችንም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አልበቃው ብሎ በሌሎች ክልሎችም የጥፋት ተላላኪዎችን  በማሰማራት ሀገር ሲያተራምስ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡

በቅርቡም በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት በመፈጸም ለዘመናት ይዞት የመጣውን ሀገር የማፍረስ ሴራ ለማሳካት መሞከሩን  እንደሚያሳይ ጠቁመው መንግስት ህግ የማስከበር ግዴታውን መወጣቱ ተገቢ ነው ብለዋል።

የትግራይ ህዝብና ህወሓት የተለያዩ ናቸው ያሉት አቶ መንግስቱ ከሞት አፋፍ ላይ ሆኖ እንኳ በከፍተኛ ወጭ የተሰሩ መሰረተ ልማቶችን ማውደሙ ህዝቡን እንደማይወክል በተግባር ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡

ቡድኑን ሥርዓት ለማሲያዝ እየተወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር ስራ በስኬት ተጠናቆ የትግራይ ህዝብ ነጻነት እንዲያገኝ ከጊዜያዊ መንግስት ጎን እንደሚቆሙ አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም