በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለውን የሕግ ማስከበር እርምጃ ሩሲያ በውስጥ የሚፈታ ችግር መሆኑን ተገንዝባለች... አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ

86

አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2013 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለውን የሕግ ማስከበር እርምጃ ሩሲያ የራስን ችግር በራስ ከመፍታት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መርህዋ የተረዳችው መሆኑን በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ ገለጹ።

አምባሳደሩ በሩሲያ የሚገኙ ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ "የህወሓት ፅንፈኛ ቡድን" ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት የሕግ ማስከበር እርምጃ እየወሰደ ይገኛል።

በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ የሕግ ማስከበሩን እርምጃ አስመልክቶ ለሩሲያ መንግስት፣ ኤምባሲው ለሚሸፍነው የአርሜኒያ መንግስት፣ በሩሲያ ለሚገኙ የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶችና ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ገለጻ መደረጉን ገልጸዋል።

በእዚህም የሕወሓት የጥፋት ቡድን ከጥንስሱ ጀምሮ በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ ሲሰራ እንደነበር ሁሉም እንዲረዱት አድርገናል ብለዋል።

በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ የደረሰው ጥቃት ቀይ መስመርን ያለፈ በመሆኑ መንግስት ወደ ሕግ ማስከበር እርምጃ እንዲገባ ማስገደዱንም አስረድተናል ብለዋል።

በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው ህግ የማስከበር እርምጃ የአገር ህልውና ጉዳይ መሆኑንም ማብራሪያ መሰጠቱን አምባሳደር አለማየሁ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ከሩሲያ መንግስት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መርሆች መካከል የራስን ችግር በራስ መፍታት በመሆኑ፤ ኢትዮጵያም በትግራይ ክልል የምታካሂደው ህግ ማስከበር የውስጥ ጉዳይ መሆኑን ሩሲያ ተገንዝባለች ብለዋል።

በተደረጉት ገለጻዎች በሩሲያ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብም በትግራይ ክልል እየተወሰደ ያለውን የሕግ ማስከበር እርምጃ ተገቢነት በአግባቡ ግንዛቤ አግኝቷል ብለዋል።

የሕግ ማስከበሩን ሂደት በተመለከተ የሩሲያው የዜና አገልግሎት "ስፑትኒክ ኒውስ" ጨምሮ በሌሎች የአገሪቷ መገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ መሰጠቱንና መረጃዎቹ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ መሰራጨታቸውንም አምባሳደሩ ተናግረዋል።

ኤምባሲው መንግስት የሕግ ማስከበር እርምጃውን አስመልክቶ በየጊዜው የሚያወጣቸውን ወቅታዊ መረጃዎች የማህበራዊ ትስስር ገጾችን በመጠቀም ኤምባሲው እያሰራጨ መሆኑንም ገልጸዋል

"በውጭ የሚኖሩ አንዳንድ 'የህወሓት ቡድን ደጋፊዎችም' የሚያስተላልፏቸውን የተዛቡ መረጃዎች በማጋለጥ ትክክለኛ መረጃ እያደረስን ነው ብለዋል አምባሳደር አለማየሁ።

በሩሲያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎችም ለሰብአዊ ድጋፍ የሚውል ገንዘብ እያሰባሰቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ባለፈ ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚከናወኑ ስራዎች ዳያስፖራዎቹ ባላቸው ሙያ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ነው አምባሳደር አለማየሁ የጠቆሙት።

በሩሲያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለሰብአዊ ድጋፍ መስጠታቸውን አብራርተዋል።

ኤምባሲው በቀጣይ በትግራይ ክልል እየተወሰደ ያለውን የሕግ ማስከበር እርምጃ አስመልክቶ ከተለያዩ ክፍለ ዓለማት የተወጣጡ ዲፕሎማቶች የሚሳተፉበት የበይነ መረብ ወይይት ለማካሄድ መታቀዱንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1898 መሆኑን መረጃች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም