"ለውጡን ትደግፋላችሁ በሚል የህወሃት ቡድን ሲያሳድዳቸው የነበሩ" የአላማጣና አካባቢው ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው እየተመለሱ ነው

62

አላማጣ፤ ህዳር 18/2013(ኢዜአ) "ለውጡን ትደግፋላችሁ በሚል የህወሃት ቡድን ሲያሳድዳቸው የነበሩ" የአላማጣና አካባቢው ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው እየተመለሱ ነው። 

በ2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በርካቶች ደስታቸውን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ገልጸዋል።

ይሁንና በአገር አቀፍ ደረጃ የመጣው ለውጥ "ትግራይ ክልልን አይነካካትም" ያለው የህወሃት ጁንታ አፈናውን አጠናክሮ መቀጠሉን ብዙዎች ይናገራሉ።

በአላማጣ እና አካባቢው ስለ ለውጥ የሚያነሳ ከተገኘ የልማት አደናቃፊ፣ የዱሮ ስርአት ናፋቂና ሌላም ስም ወጥቶለት ለሞት ወይም እስራት እንደሚዳረግ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

በዚህም ከአላማጣና አካባቢው የህወሃትን እስራትና ግድያ በመሸሽ ላለፉት ሁለት አመታት ከአካባቢያቸውና ከቤተሰባቸው ርቀው የቆዩ ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው መመለስ ጀምረዋል።

ከህወሃት እይታ ተሰውረው በተለያዩ አካባቢዎች ቆይተው ወደ አላማጣ ከተመለሱት የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት እንዳሉት የአገር መከላከያ ሰራዊት ባከናወነው ህግ ማስከበር ጁንታው በመበተኑ ወደ ቀያቸው እና ቤተሰቦቻቸው ተመልሰዋል።  

እንደ አስተያየት ሰጭዎቹ ገለፃ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመጣውን ለውጥ መደገፍ በህወሃቶች ዘንድ "ወንጀል ሆኖ በመቆየቱ" ከአካባቢው ለመሰደድ ችለዋል።

በጽሁፍ ለሚያቀርቧቸው አግባብነት ያላቸው ጥያቄዎችም ህወሓት ወንጀል አድርጎት ለእስራትና ግርፋት ሲፈልገን አካባቢውን ለቀናል ነው ያሉት።

"የህወሃት ቡድን በራያ ምድር የሚፈልገው ሃብትና መሬት እንጂ ስለ ዜጎች አያስብም" የሚሉት አስተያየት ሰጭዎቹ በርካቶችን በእስራትና አፍኖ በመውሰድ ሲያሰቃያቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን ላይ ግን የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ በአካባቢው ላይ ህግ በማስከበሩና ጁንታው በመበታተኑ ደስታ ተሰምቶናል፤ ሰላምና መረጋጋትም እየተፈጠረ ነው ብለዋል።

የህወሃትን የጥፋት ቡድን በማጋለጥና ጥፋተኞች ለህግ አንዲቀርቡ በማድርግ መንግስት ለሚያከናውነው ስራ ከጎን በመቆም እንደሚደግፉም አረጋግጠዋል።

የሕግ የማስከበር ሥራው እስኪጠናቀቅ በተለይ ወጣቱ ተደራጅቶ ከመንግስትና ከፀጥታ ሃይሉ ጎን እንዲቆምም ጠይቀዋል።

በተለይ የራያ እና አካባቢው ህዝብ ባለፉት 30 ዓመታት በህወሓት አፈና እና ግፍ ብዙ በደል አንደደረሰበት አስታውሰው፤ሕዝቡ ከመከላከያ ሰራዊቱና ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ተቀናጅቶ ለአካባቢው ሰላምና ፀጥታ መስፈን በጋራ እንደሚሰራ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የአላማጣ ከተማና አካባቢው በቅርቡ ከጁንታው አፈና እና እንግልት ነፃ መውጣቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም