በአርባምንጭ ከተማ ሁከት ለማስነሳት የተደረገው ሙከራ መክሸፉ ተገለፀ

62
አርባምንጭ ሀምሌ 11/2010 በአርባምንጭ ከተማ ከሁለት ቀበሌዎች ተውጣጥተው በቡድን በመደራጀት ሁከት ለማስነሳት ያደረጉት ሙከራ በህብረተሰቡና በፀጥታ ኃይሎች ጥረት መክሸፉን የጋሞ ጎፉ ዞን ፀጥታ አስተዳደር መምሪያ አስታወቀ። የመምሪያው ኃላፊ አቶ ቤታ አንጁሎ ትናንት ለኢዜአ እንደተናገሩት ሐምሌ 2 ቀን 2010 አገራዊ ለውጡን ለመደገፍ በከተማው በተካሄደው ሰልፍ አመራሩን የገጠመውን ተቃውሞ ተከትሎ "ከተማውን የሚያስተዳድር የለም" በሚል የተሳሳተ ቅስቀሳ ሲካሄዱ ቆይተዋል። በዚህ ቅስቀሳ ከሁለት ቀበሌ የተደራጁ ቡድኖች ትናንት ረፋድ ላይ በፈጠሩት ሁከት የከተማው እንቅስቃሴ በተወሰኑ አካባቢዎች ተስተጓጉሎ እንደነበረ ገልጸዋል። ሁከቱን ከተማ አቀፍ ለማድረግና በንብረት ላይ ጉዳት ለማድረስ መንገድ የመዝጋትና ዝርፍያ የማካሄድ ሙከራዎች መደረጋቸውንም ተናግረዋል። ሆኖም የከተማው ነዋሪ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ባደረጉት ጥረት ሙከራው በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት ሳያደርስ መክሸፉን ገልጸዋል። በድርጊቱ የተሳተፉ አካላት በቁጥጥር ስር ውለው ፖሊስ ምርመራ በማድረግ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል። ከዚህም ሌላ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ አመራር ለተገኙ አገራዊ ለውጦች እውቅና ለመስጠት በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች የድጋፍ ሰልፍ በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ "አንዳንድ አካባቢዎች ሰልፎችን በማስታከክ ሁከት የማስነሳት አዝማሚያዎች እየታዩ ነው" ያሉት አቶ ቤታ ከሰልፉ ዓላማ ውጭ ሁከት ለማስነሳት የሚደረጉ ሙከራዎችን ህብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመሆን ሊመክተው እንደሚገባም ጠይቋል። ከነዋሪዎቹ መካከል የወዜ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ስምኦን ታዬ በሰጡት አስተያየት አርባምንጭ ከተማ ሁከት እንዲፈጠር አቅዶ የሚቀሰቅሱ ግለሰቦችና ቡድኖች መኖራቸውን ገልጸዋል። ወጣቱ ከሁከቱ ራሱን እንዲጠብቅ ወላጆች ፣ ቤተሰቦችና መንግስት ሊመክራቸው እንደምገባም ገልጸዋል። የሴቻ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ፀሐይ ለማ በበኩላቸው "ከወጣቶች በላይ ከተማዋ እንዳትረጋጋ የሚያደርጉ አዋቂ ግለሰቦች አሉ" ብለዋል፡፡ በማህበራዊ ሚዲያ በሚለቀቁ ለማንም በማይበጁና አካባቢውን የሚጎዱ የጥላቻ መልዕክቶች ወጣቱ እንዲሳተፍ የሚቀሰቅሱ አካላት መጠየቅ እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡ የህግ የበላይነትን ለማስከበር በሚደርጉ ጥረቶች የድርሻቸውን እንደሚወጡም አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም