መገናኛ ብዙሃን ሰብዓዊ መብት ላይ ያተኮሩ ዘገባዎችን በስፋት መሥራት አለባቸው --ኮሚሽኑ

67

አዲስ አበባ ህዳር 16 /2013 (ኢዜአ) መገናኛ ብዙሃን ለሰብዓዊ መብት መከበርና መጠናከር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የዘገባ ሥራዎችን በስፋት መሥራት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለፀ።

ኮሚሽኑ ታህሳስ 1 ቀን 2013 ዓም የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ቀን በማስመልከት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና መገናኛ ብዙሃን ያላቸውን አጋርነት አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ጋር ዛሬ ውይይት አካሂዷል።

በኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብት ክትትልና ጥበቃ ከፍተኛ አማካሪ አቶ ምስጋናው ሙሉጌታ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ልዩ ልዩ የሰብዓዊ  መብት  ጥሰቶች  ሲፈጸሙ ይስተዋላል።  

በአገሪቱ እየታየ ካለው የፖለቲካ ሽግግር ጋር በተያያዘ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በተለያዩ አካላት መፈጸማቸውንም ነው የተናገሩት።

“አሁን በተለይ ከፖለቲካ ሽግግሩ ጋር ተያይዞ እጅግ አሳሳቢና ሰቅጣጭ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲከሰቱ ተስተውሏል፣ በጣም አንገት የሚያስደፉ፤ በጣም የሚያሳፍሩ” በማለትም የችግሩን ስፋት አንስተዋል።

በየጊዜው እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማስቆምና  ሰብአዊ መብቶችን  ለማስከበር ኮሚሽኑ ብቻውን ውጤት ማምጣት እንደማይችልና ለዚህም የሁሉም አካላት ትብብር አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በተለይም መገናኛ ብዙሃን ለሰብዓዊ መብት መከበርና መጠናከር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ዘገባዎችን በማስፋት የሰብዓዊ መብትን ያከበረ የፖለቲካ ባህል እንዲገነባ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው አቶ ምስጋናው ተናግረዋል።

በሰብዓዊ መብት አያያዝ ጠንካራ ጎኖችንና ክፍተቶችን መለየት፣ በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ንጽጽራዊ ትንተና መስጠት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ልምዶችን መቀመር እንደሚገባም ነው የገለጹት።  

መገናኛ ብዙሀን ዓለም አቀፍ ተቋማት በዘርፉ የሚያወጧቸውን ምክረ  ሃሳቦች  መተንተን፣  መንግስት ግዴታውን እየተወጣ ስለመሆኑ መቆጣጠር እንዲሁም ጥሰቶች  ሲፈጸሙ በአግባቡ መመርመርና ማጋለጥ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።  

በተለይ በሰብዓዊ መብት ላይ ያተኮሩ ዘገባዎች ቁጥርና ጥራትን መጨመር እንደሚገባ ጠቁመው ለእዚህም ጋዜጠኞች ከከተማ ወጣ በማለት  ተጨባጭ  ጉዳዮችን መዳሰስ  እንዳለባቸው አሳስበዋል።   

"የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቅሬታዎችን መጠቆም፣ መዘገብ፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ የሚያተኩር የምርመራ ጋዜጠኝነት እንዲሁም በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚሰሩ ጋዜጠኞችን ማፍራት ይገባልም" ብለዋል።

ከዘርፉ ተቋማት ጋር ተቀራርቦ መሥራት፣ የጋራ አጀንዳ መቅረጽ፣ በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚሰሩ ተቋማት ሥራዎችን ተከታትሎ መዘገብ እንዲሁም  መወትወትና  ተጠያቂነትን  ማስፈን እንደሚገባም አቶ ምስጋናው አመልክተዋል።     

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም