በጎንደር ከተማ የጁንታውን ተልዕኮ ለማስፈፀም ሲንቀሳቀሱ የተገኙ 44 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

60

ጎንደር፤ ህዳር 16/2013(ኢዜአ)በጎንደር ከተማ የህወሃት ጁንታን የጥፋት ተልዕኮ አስፈጻሚ በመሆን ሲንቀሳቀሱ የተገኙ 44 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የከተማ አሰተዳደሩ የሠላምና ህዝብ ደህንነት መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ናትናኤል ጎሹ ለኢዜአ እንደተናገሩት ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ሥር ማዋል የተቻለው በከተማው ነዋሪዎች ጥቆማ እንዲሁም  የፀጥታ ሃይሉ ባደረገው ክትትልና ቁጥጥር  ነው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ  በጎንደር ከተማ ጥፋት ለማድረስ ከጁንታው ተልዕኮ ተቀብለው በመረጃ ልውውጥ ሲሰሩ የተገኙ እንደሆኑም ተጠቅሷል።

ከፌደራል፣ ከክልልና ከከተማ አስተዳዳሩ ተውጣጥቶ የተቋቋመው መርማሪ አካል ቁጥጥር ሥል በዋሉት ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ እያደረገባቸው መሆኑንና  ጉዳያቸው ተጣርቶ ለህግ እንደሚቀርቡም አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም 96 ተጠርጣሪዎች ተይዘው  አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎባቸው በጊዜያዊነት በዋስ መለቀቃቸውን ጠቁመዋል፡፡

የከተማዋን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ በኩል የተለያዩ አደረጃጃቶችን በመጠቀም ህዝቡን ያሳተፈ የጸጥታ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ያመለከቱት ሃላፊው፤ ህብረተሰቡ ከፀጥታ ሃይሉ ጋር የጀመረውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡

የከተማዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ አግማስ በበኩላቸው ጁንታው  ሀገር የማፍረስ ተግባሩን ለማሳካት ከከፈተው ጦርነት ጀርባ የጥፋት ተልዕኮ በሰጣቸው ጭምር እየተፍጨረጨረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የጎንደር ከተማን ሰላም ለማደፍረስ በቅርቡ የሮኬት ጥቃት መፈጸሙን ያስታወሱት ምክትል ከንቲባው የጥፋት ቡድኑ በቁጥጥር ሥር እስኪውል ድረስ ከጥፋት ወደኋላ እንደማይል ተናግረዋል፡፡

ህግ ለማስከበር በግንባር ለሚገኘው ሃይል የከተማው ነዋሪ ህዝብ እያደረገ ያለውን የደጀንነት ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም