የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት መሻሻል ለአፍሪካ ቀንድ ዕድገትና መረጋጋት ወሳኝ ድርሻ አለው...የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

66
ድሬዳዋ አምሌ11/2010 ኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነታቸውን ማሻሻላቸው ለአገራቱና ለምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ መረጋጋትና የምጣኔ ሃብት ዕድገት ወሳኝ ድርሻ እንደሚኖረው የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካና የምጣኔ ሃብት መምህራን ገለጹ። ምሁራኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የጀመሯቸው የለውጥ ተግባራት እንዲሳኩ ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ፣ የፖለቲካ፣ የሥነ-ምግባርና የሲቪክስ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያዎችና መምህራን ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ የፈጠሩት ስምምነት ለአገራቱ ዕድገት፣ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ኃላፊና መምህር የሆኑት አቶ ፉጂ ጫላ እንዳሉት ባለፉት 20 ዓመታት ሁለቱ አገሮች አንዱ አንዱን ሲያዳክምና ሲወነጅል ቆይቷል። ሲፈጥሩት በነበረው የፕሮፖጋንዳ ጦርነትም በአገራቱ መካከል ውጥረት እንዲነግስ ከማድረግ ባለፈ በቀጠናው አገራት አለመረጋጋት ተፈጥሮ መቆየቱን አስታውሰዋል። በአሁኑ ወቅት አገራቱ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ቅሬታቸውን በራሳቸው ፈተው ያቋረጡትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መቀጠላቸው በዓለም አቀፍ ጭምር በአርአያነት የሚታይ መሆኑን ገልጸዋል። " የደረሱበት ስምምነት በሁለቱ አገሮች ዘላቂነት ያለው ሰላም እንዲሰፍን ያግዛል፣ ከእዚህ ባለፈ ለምስራቅ አፍሪካ አገራት መረጋጋትና ለጋራ ዕድገት አስተዋጽኦ የጎላ ነው " ሲሉም አቶ ፉጂ አመልክተዋል፡፡ እንደ መምህር ፉጂ ገለጻ መንግስት በዓለም አቀፍ የፖለቲካ መርህ ከጦርነት ይልቅ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የተሻለ አዋጭ መሆኑን በተግባር እያሳየ በመሆኑ በቀጣይ የአገሪቱን ዕድገትና ተቀባይነት ያጎላዋል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት የተጀመሩ የለውጥ እንቅስቃሴዎች የሚፈለገውን ውጤት እንዲያስገኙ "ሕብረተሰቡ የህግ የበላይነት በማክበር ሰላሙን መጠበቅና ሙሁራንም በጥናትና በምርምር ሥራዎች የበኩላችንን ድጋፍ ልናደርግ ይገባል" ብለዋል፡፡ የአቶ ፉጂን ሃሳብ የተጋሩት የኢኮኖሚክስ መምህር አቶ ፋሚ አባስ በበኩላቸው የአገራቱ ግንኙነት መጠናከር የባህር በር ለሌላት ኢትዮጵያ ወሳኝ ጥቅም እንደሚኖረው ገልጸዋል። " ሁለቱ አገሮች በኢኮኖሚው መስክና በንግድ ግንኙነታቸው እንዲያድግና በዓለም የንግድ ድርጅት ውስጥ ያላቸው ተሰሚነት እንዲጎለብት ጭምር ግንኙነቱ አስተዋጽኦው ወሳኝ ነው" ብለዋል፡፡ ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮ ተመራቂዎች መካከል ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የወርቅ ተሸላሚ የሆነችው መድኃኒት ፉአድ በበኩሏ የአገራቱ ግንኙነት መሻሻል ኢትዮጵያ በቅርብ ርቀት አማራጭ ወደቦችን እንድታገኝ የሚያስችላት መሆኑን ተናግራለች። በዶክተር አብይ የሚመራው መንግስት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ጨምሮ በአገር ውስጥም ታላቅ ተስፋን የሰነቀ እንቅስቃሴ እያከናወነ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የሲቪክስና የሥነ-ምግባር ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ደሳለኝ አበራ ናቸው፡፡ እንደባለሙያው ገለጻ ሁለቱ አገሮች በራሳቸው ተነሳሽነት ያቋረጡትን ግንኙነት መቀጠላቸው ለሁለቱ አገሮች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዕድገት የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ከሁለቱ አገራትና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ የሚፈለገው ተጠቃሚነት እንዲመጣና የተጀመረው አገራዊ ለውጥ ዳር እንዲደርስ ህዝቡ ቅድሚያ ለሰላሙ  ዘብ መቆም እንዳለበት አመልክተዋል ፡፡ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ሄኖክ ጌታነህ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አገሪቱን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ የተፈጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። "ይህ ሀሳባቸው እንዲሳካና የለውጥ ጅማሮው በዘላቂነት ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ሊደግፋቸው ይገባል" ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም