በአዲስ አበባ በመሬት ወረራና ህገ ወጥ ግንባታ የጥናት ግኝት ላይ ተመስርቶ እርምጃ ሊወሰድ ነው

142

አዲስ አበባ ህዳር 16/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ባለው የመሬት ወረራና ህገ ወጥ ግንባታ የጥናት ግኝት ላይ ተመስርቶ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ምክት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

ምክትል ከንቲባዋ በመንግስት ተቋማት ውስጥ 'ጠቅሜ ልጠቀም' በሚል በህገ ወጥ ድርጊቶች ላይ የሚሳተፉ አመራሮች ካሉ ከድርጊታቸው ይቆጠቡ ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ 1 ሺህ 352 ሄክታር መሬት በህገ ወጥ መልኩ መወረሩን፤ 79 ሺህ 114 ህገ ወጥ ግንባታዎች መከናወናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በዚህም የከተማ አስተዳድሩ በትንሹ 14 ቢሊዮን ብር ማጣቱ ነው የሚነገረው።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በህገ ወጥ መንደሮች 76 ነጥብ 8 ሚሊዮን፣ በግለሰቦች 2 ሚሊዮን፣ በባለሃብቶች 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን እንዲሁም የልማት ቦታዎችን በማስፋፋ 505 ሺህ 706 ካሬ ሜትር ቦታ ተወሯል።

በተጨማሪም በሪል ስቴት ባለሀብቶች 184 ሺህ 208፣ በሃይማኖት ተቋማት 976 ሺህ እና በመንግስት ተቋማት 467 ሺህ 774 ካሬ ሜትር ቦታ በህገ ወጥ መልኩ መወረሩ ታውቋል።

በዚህም የተሰረዙ ካርታዎችን ማደስ፣ በሪል ስቴት ስም ለግለሰቦች መሬት መስጠት፣ የመንግስት ቤቶችን ማፍረስና ሰነድ ማጥፋት እንዲሁም የአርሶ አደሩን መሬት ወደ መሬት ባንክ ማስግባት የድርጊቱ ባህሪያት እንደነበሩም ተገልጿል።

መረጃው የሚያመለክተው ከ1997 አስከ 2010 እና ከ2010 አስከ 2012 በሚል በሁለት ተከፍሎ የተደረገውን የጥናት ግኝት ነው።

በመሬት ወረራው ላይ የጸጥታ አካላት፣ ዳላሎች፣ ባለሀብቶች፣ የመንግስት አመራሮች የተሳተፉበት መሆኑም ተመላክቷል።

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በጥናቱ ግኝት ላይ ተመስርቶ ለችግሩ እልባት መስጠት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርገዋል።

ምክትል ከንቲባዋ በንግግራቸው የጋራን ሃብትን በጋራ በመጠቀም ማልማት እንጂ ተጠቃሚ እና ተጎጂ መኖር የለበትም ብለዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የተሳተፉ የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች በቤተ አምነቶች ስም የሚደረግ የመሬት ወረራን እንደሚኮንኑ ገልጸዋል።

በመንግሰት በኩል በሃይሞኖት ተቋማት ዘንድ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ አለመስጠቱ ግን ለችግር በር መክፈቱን አመላክተዋል።

የትምህርት፣ ጤናና መሰል ማህበራዊ አገልገሎት መስጫ ተቋማትን ጨምሮ በአዳዲስ መንደሮች የነዋሪዎች የማምለኪያ ሥፍራ ጥያቄዎች እንዲሟሉ ቃል የተገባው መሰረት ምላሽ መሰጠት ይኖርበታልም ብለዋል።

የሃይማኖት ጉዳይ ስስ በመሆኑ ከእርምጃው በፊት ከየእምነቱ አባቶች ጋር በመመካከር ለችግሩ እልባት መስጠት እንደሚገባም ተሳታፊዎች አመልክተዋል።

ምክትል ከንቲባዋ በምላሻቸው ቤተ እምነቶች የሚገጥሟቸው የቢሮክራሲ አሰራሮች ይፈታሉ ብለዋል።

ይሁን እንጂ ለማህበረሰቡ የሞራል ተምሳሌት በሆኑ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ አንዳንድ ግለሰቦች የተቋማት ስም እንዲጎድፍ እያደረጉ መሆኑን አመልክተዋል።

የመሬት ወረራን በተመለከተ በጥናት በግኝቱ ላይ ተመስርቶ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ገልጸው የህግ ማስከበሩን ሥራ ለማደናቀፍ የሚሹ አካላት እጃቸውን እንዲሰበስቡ ጠይቀዋል።

"ህግ የማስከበር ሥራው ህብረተሰቡን ባሳተፈ አግባብ ተፈጻሚ ይሆናልም" ብለዋል።

በከተማዋ ህገ ወጥነትን በማስወገድ ህጋዊነትን ማስፈን የመንግስት ውሳኔ መሆኑን ገልጸው፤ ሁሉም አካል ለውሳኔው ተግባራዊነት አንድ አቋም ይዞ እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል 'ጠቅሜ ልጠቀም' በሚል ከወንጀለኞች ጋር የሚተባበሩ የመንግስት አመራሮች ከደረጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር አባይ "ምርጫችን ህገ ወጥነት አልያም የሚከፈል መስዋዕትነት ከፍሎም ህግና ስርዓት ማስያዝ ነው" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ለችግሩ እልባት ለመስጠት በመንግስት የሚወሰደው የመፈትሄ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም