የማህበራዊ ጤና መድህን አላማን ለህብረተሰቡ ለማስረጽ መገናኛ ብዙሃን ትኩረት ሊሰጡ ይገባል --ኤጀንሲው

60

አዳማ ህዳር 16/2013 (ኢዜአ) ዜጎች በዝቅተኛ ወጪ የተሻለ ህክምና የሚያገኙበትን የማህበራዊ ጤና መድህን አላማ ለህበረተሰቡ ለማሰረጽ የመገናኛ ብዙሃን ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ የማህበራዊ ጤና መድህን ኤጀንሲ አስታወቀ። 

ኤጀንሲው ከግልና ከመንግሥት መገናኛ ብዙሀን ተቋማት ለተወጣጡ የዘርፍ ባለሙያዎች በቀጣይ በትብብር መስራት በሚቻልበት ሂደት ላይ ትላንት በአዳማ መክሯል።

የኤጄንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አለሙ አኖ በወቅቱ እንደገለፁት በሀገሪቱ  ከስምንት አመት በፊት የተጀመረው  የማህበራዊ ጤና መድህን አገልግሎት ከ770 በላይ በሚሆኑ ወረዳዎች ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

ዜጎች በዝቅተኛ ወጪ የተሻለ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙና እንደፍላጐታቸው እንዲስተናገዱ የጤና መድህን ስርዓት መዘርጋቱን ገልጸዋል።

የአገልግሎት ስርዓቱ እንዲጠናከርና ቀልጣፋና ጥራት ያለው እንዲሆን በኤጀንሲው እየተደረገ ያለውን ጥረት የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች እንዲያግዙ ምክክሩ ማስፈለጉን ጠቅሰዋል።

"ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ሽፋን አርሶ አደሩን፣ አርብቶ አደሩንና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ያደረገ ነው" ብለዋል።

አገልግሎቱ ተግባራዊ በሆነባቸው 770 በላይ ወረዳዎች ከ 6 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ አባ ወራና እማ ወራዎችን በአባልነት ማቀፍ መቻሉን የገለፁት አቶ አለሙ ከ30 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመት ተጨማሪ በ127 ወረዳዎች አገልግሎቱን ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጀምሮ ዘርፉን ማገዝ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ህብረተሰቡም የመርሀ ግብሩን አላማ በሚገባ አውቆ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል ተቋማቱ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ አመላከተዋል ።

ውል በተገባባቸው የጤና ተቋማት ከመድሃኒትና የህክምና መርጃ መሳሪያዎችን ጨምሮ የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶች መኖራቸውን የገለፁት ደግሞ በኤጀንሲው የአባላት ምዝገባና መዋጮ ዳይሬክተር አቶ ጉደታ አበበ ናቸው።

ከሀገሪቷ ጠቅላላ ህዝብ 24 በመቶ የሚሆነው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኝና በቀጥታ ከፍሎ መታከም የማይችል መሆኑን ጠቁመዋል።

ባለፈው ዓመት ከአባላት ከተሰበሰበው ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ውስጥ 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብሩ ውል ለተገባላቸው ከ2ሺህ 800 በላይ ለሚሆኑ የጤና ተቋማት መከፈሉን ተናግረዋል።

በምክክር መድረኩ ከተሳተፉ መገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች መካከል የኢቢኤስ ቴለቪዥን ተወካይ ጋዜጠኛ ገነት ዴንስሞ "የጤና መድሀን አባላት ተገቢውን የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ ከኤጀንሲው ጋር እንሰራለን" ብላለች።

በመርሀ ግብሩ የታቀፉ አባላት በዝቅተኛ ወጪ ከጤና ጣቢያ እስከ ከፍተኛ ህክምና ድረስ አገልግሎት የሚያገኙ ቢሆንም ህብረተሰቡ ዘንድ የግንዛቤ ክፍተት መኖሩን ገልፃለች።

"ህብረተሰቡ የጤና መድህን ዋስትና መያዙ በስሩ ላሉ ልጆቹና ቤተሰቡ የጤና አገልግሎት የሚያገኝበት ነው" ያለው ደግሞ የዋልታ ቴለቪዥን ተወካይ ጋዜጠኛ ሳሙኤል ዳኛቸው ነው።

"በመርሀ ግብሩ ዙሪያ ህብረተሰቡ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው በዘላቂነት እንሰራለን" ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም