አለም አቀፉ ህብረተሰብ በማይካድራ የተፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ እንዲያወግዝ ተጠየቀ

47

ህዳር 15/2013 (ኢዜአ) አለም አቀፉ ህብረተሰብ በማይካድራ የተፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ እንዲያወግዝ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ጥሪ አቀረበ።

የፌደራል መንግስት በማይካድራ በህወሃት ቡድን የተፈጸመውን ግድያ አውግዟል።

በማይካድራ የተፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ በተመለከተ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የወጣው ሪፖርት ልብን የሚያደማ መሆኑን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።

ሪፖርቱ ቀደም ሲል በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የወጣውን መረጃ ያረጋገጠ ነው ተብሏል።

በኮሚሽኑ እንደተገለጸው የማይካድራው ጥቃት ተራ ወንጀል ሳይሆን ታቅዶና ሆነ ተብሎ በጥንቃቄና በቅንጅት  የተፈጸመ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑም ተመልክቷል።

በዚህም በኢትዮጵያ በህወሃት የጥፋት ቡድን እየተፈጸሙ ያሉ አሰቃቂ ወንጀሎች የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማየት ችሏል ነው የተባለው።

ግድያው በእቅድና በሙሉ ዝግጅት የተከናወነ በርካታ ቁጥር ያላቸው ንጹሃን ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መሆኑም ተጠቅሷል።

የህወሃት ደህንነት ሀይሎች ከ ‘ሳማሪ’ ከተሰኘ የህወሃት የወጣቶች ቡድን ጋር በመሆን በመቶዎች  የሚቆጠሩ ሰዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደሉም ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እንደተገለጸው ይህ ከባድ ወንጀል  በሰብዓዊ መብት ጥሰትና የጦር ወንጀለኛነት የሚያስጠይቅ እንደሆነ ተብራርቷል።

ይህንን ጸረ ሰብዓዊ የሆነ አስከፊ ወንጀል የአለም አቀፉ ህብረተሰብ  እንዲያወግዝና መንግስት እነዚህን ወንጀለኞች በፍርድ ከመጠየቅ ወደ ኋላ እንደማይል ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም