የኢትዮ-ቻይና የ50 ዓመታት ወዳጅነትና መተማመን በጽኑ መሰረት ላይ ተገንብቷል

69

አዲስ አበባ፣ ህዳር 15/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያና ቻይና የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመሩበትን 50ኛ ዓመት በማክበር ላይ ይገኛሉ፤ የአገራቱ ወዳጅነትና መተማመን በጽኑ መሰረት ላይ መገንባቱ ተነግሯል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ የዲፕሎማሲ ግንኙነቱ የተጀመረበትን 50ኛ ዓመት በማስመልከት ባደረጉት የቪዲዮ ምክክር የሁለቱ አገራት ወዳጅነትና መተማመን ባለፉት 50 ዓመታት በጽኑ መሰረት ላይ መገንባቱን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያና ቻይና በአምባሳደር ደረጃ ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመሩት እ.አ.አ 1970 ሲሆን ከዚህ ጊዜ ጀመሮ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት የሆኑት ሁለቱ አገራት ትብብራቸውን ገፍተውበታል።

የአገራቱ ታሪካዊ ልምድና ተመሳሳይ የልማት ጉጉት ትብብራቸውን በጥብቅ ያቆራኘው ሲሆን እድገታቸውንም በጋራ ፍላጎት ወደፊት እያራመዱት ነው፡፡

ባለፉት 50 ዓመታት ዓለም በእጅጉ ብትለዋወጥም ሁለቱ አገራት በእኩልነት መንፈስና በመከባበር አጋርነታቸውን አጠናክረው ገፍተውበታል፤ የእድገት ጉዟቸውንም ብሄራዊ ጥቅምን መሰረት ባደረገ ሁኔታ እየተገበሩት ነው፡፡

በጋራ መግባባት ላይ በመመስረት ቅድሚያ የሚሰጡትን ዘርፍ በመለየት በጋራ እሳቤ፣ በእኩልነትና በፍትሃዊነት እየከወኑትም ነው፡፡

አጠቃላይ የሆነ ስትራቴጂካዊ አጋርነትን በማጽናት አገራቱ ግንኙነታቸውን ከማሳደጋቸውም በላይ የስትራቴጂዎቹን ጠቀሜታ በመለየት ትብብራቸውን ቀጥለውበታል፡፡

አሁናዊው የኢትዮጵያና ቻይና ግንኙነት ከቀደመው የተሻለ ጠንካራ መሰረት ይዟል፤ አገራቱ የፖለቲካ መተማመናቸውን በማጎልበት በጋራ ወደፊት እየተጓዙ ነው፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአገራቱ መሪዎች በተደጋጋሚ በመገናኘት በርካታ ምክክሮችን አካሂደዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂን ፒንግ በይፋዊ መንገድ ሁለት ጊዜ በመገናኘት ሰፋ ባሉ ጉዳዮች ላይ የመከሩ ሲሆን በርካታ የስልክ ውይይትና የቪዲዮ ኮንፈረንስ አከናውነዋል፤ በመልዕክተኞች አማካኝነትም ሃሳብ ተለዋውጠዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ እ.አ.አ በ2018 በቤጂንግ በተካሄደው የቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም ጉባኤ በመገኘት ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን እ.አ.አ በ2019 በተከናወነው ሁለተኛው የቤልት ኤንድ ሮድ ጉባኤ በመሳተፍ ቀጣይ ጉብኝታቸውን አከናውነዋል፡፡

በቀደመው ዘመን ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ቻይናን በመጎብኘት ከሊቀ መንበር ማኦ ዚዶንግ ጋር ተወያይተዋል፡፡

የቀደሙት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትሮችም ተደጋጋሚ፣ ቀጣይነት ያለው ግንኙነታቸውን የሚያስተሳስሩና የቅርብ አጋርነታቸውን የሚያጠናክሩ ጉብኝቶችን በቻይና አድርገዋል፡፡

በከፍተኛ አመራሮች የሚደረጉት ተከታታይ ግንኙነቶች የአገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ከፍ ወዳለ ደረጃ አሸጋግሮታል፡፡

ተመሳሳይ ደረጃ ያላቸውና ወደኋላ የቀሩት ሁለቱ አገራት በሉላዊነት ዘመን የገጠማቸውን የአየር ፀባይ ለውጥ፣ ድህነት ቅነሳና ቀጣናዊ ግጭት ለመፍታት ከተባበሩት መንግስታትና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅርበት በመገናኘትና በመተባበር በማደግ ላይ የሚገኙ አገራትን የጋራ ፍላጎት እውን ለማድረግና ለመጠበቅ በንቃት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ 

አገራቱ በመተባበር ከድንበራቸው የተሻገረ ውጤታማ ፍሬ ማፍራታቸው ተገልጿል፤ ቻይና የኢትዮጵያ ቀዳሚ የንግድ አጋር፣ የኢንቨስትመንት ምንጭና የልማት አጋር ናት።

እ.አ.አ ከ2000 እስከ 2019 የሁለትዮሽ የንግድ ሚዛን በ26 በመቶ ጨምሯል፤ የኢትዮጵያ ቡናና አበባ በቻይና ገበያ ዝናን ተቀዳጅተዋል፤ ከኢትዮጵያ የሚላከው የሰሊጥ ምርትም በቻይና ካለው ፍላጎት አንድ አስረኛውን ይሸፍናል፡፡

ስራ የጀመሩና በመገንባት ላይ የሚገኙ 1 ሺህ 500 የቻይና ኩባንያዎች ድምር ኢንቨስትመንት 1 ነጥብ 153 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የደረሰ ሲሆን ከ60 ሺህ ለሚልቁ ኢትዮጵያዊያን የስራ ዕድል አስገኝተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ የትብብር ስምምነትን ከቻይና ጋር በቅድሚያ ከተፈራረሙ የአፍሪካ አገራት አንዷ ናት፡፡

የአዲስ አበባ-ጅቡቲ የባቡር መስመር የቤልት ኤንድ ሮድ የትብብር ስምምነት ማሳያ ዋነኛ ፕሮጀክትም ነው፡፡

መንገዶች፣ አየር ማረፊያዎች፣ የኢንዱስትሪ ዞኖች፣ የኃይል ማመንጫዎችና መሰል የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በትብብሩ በመታገዝ የተገነቡ ሲሆን የኢትዮጵያን ቀጣይነቱ የተረጋገጠ የእድገት ጉዞ በማሳለጥ በኩል የማይተካ ሚና ተጫውተዋል፡፡

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2019 በቻይና በመታገዝ የመጀመሪያ ሳተላይቷን ወደ ጠፈር ያመጠቀች ሲሆን በአገራቱ መካከል በሳይንስና ቴክኖሎጂ ትብብር ፈር ቀዳጅ የሆነ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

የቻይና ቱሪስቶች ለኢትዮጵያ የጉዞና የቱሪዝም ዘርፍ እድገት ያበረከቱት ድርሻ የላቀ መሆኑም ይታመናል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድም ከየትኛውም የአፍሪካ አየር መንገድ በላቀ ወደ ቻይና የሚያደርገው የበረራ ትስስር ከፍ ያለውን ቁጥር በመያዙ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ከማሳደጉ ባለፈ በአፍሪካና በቻይና መካከል ላለው የአየር ጭነት የንግድ አገልግሎት ማደግ አይነተኛ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡

የሁለቱ አገራት አመራሮች ያላቸው የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ የተጠና ፖሊሲና ለቻይና የገንዘብ ተቋማትና ኢንተርፕራይዞች የሚሰጡት ግምት ዓለም ዓቀፍ አመለካከቱ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲያደግ አስችሎታል፡፡

በዚህም በሁሉም ዘርፍ ሁሉንም አሸናፊ ያደረገ ውጤት መመዝገብ ችሏል፡፡

ሁለቱ አገራት በጊዜ ሂደት ያዳበሩትና ክብር የተቸረው ስልጣኔያቸው እርስ በእርስ በመማማር ላይ ፀንቶ የቆመ ነው፣ በባህል፣ በትምህርት፣ በጤናና በቱሪዝም ዘርፍ ያለው ትብብርም ከፍ ወዳለ ደረጃ ተሸጋግሯል፡፡

የኮንፊሺየስ ኢኒስቲቲዩት፣ የሕክምና ቡድን፣ ተማሪዎች፣ በጎ ፈቃደኞችና እህትማማች ከተሞች በሁለቱ ሕዝቦች መካካል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር በኩል ቀዳሚውን ድርሻ ይዘዋል፡፡

የአዲስ አበባ የወንዝ ዳር አረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት በቻይና ድጋፍ እየተገነባ ሲሆን ከተማዋ ውብና ምርጥ የቱሪዝም መዳረሻ ለመሆን የያዘቸውን ግብ እውን ለማድረግ ተጨማሪ አቅም ይሆናታል፡፡

በርካታ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ወደ ቻይና በመመላለስ ላይ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ቀደምት ባህል በቻይና አባወራዎች ዘንድ በስፋት የሚተረክ ሲሆን በተመሳሳይ የቻይና ኩንግፉ በኢትዮጵያ ወጣቶቸ ዘንድ ተወዳጅነቱ ከፍ ያለ ሆኗል፡፡

ቻይናና ኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሸኝን ለመግታት ውጤታማ ትብብር አከናውነዋል፡ ፡ፕሬዚዳነት ሳህለወርቀ ዘውዴ እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቻይና የተከሰተውን ወረርሽኝ አስመልክተው የተሰማቸውን ሃዘን ደብዳቤ በመላክ ለፕሬዚዳንት ዢ ጂን ፒንግ ገልጸውላቸዋል፡፡

ቻይና ወረርሽኙን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት ኢትዮጵያ እንደምትደግፍና አጋር ሆና እንደምትቆምም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስልክ በመደወል ለፕሬዚዳንቱ አረጋግጠውላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድም ኮቪድ ከተከሰተ በኋላ ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ ሳያቋርጥ በመቀጠል ቁርጠኝነቱን ያስመሰከረ ሲሆን ወደ አፍሪካና የተቀረው ዓለም የሚላከውን የኮቪድ መከላከያ ቁሳቁስ በማጓጓዝ ቁልፍ ሚናውን ተወጥቷል፡፡

የቻይና መንግስት በብሄራዊና በክልል ደረጃ እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች በሚንቀሳቀሱ ማህበራት አማካኝነት ኮቪድ ከተከሰተ አንሰቶ ለኢትዮጵያ በርካታ ድጋፎችን አድርጓል፡፡

የቻይና የሕከምና ኤከስፐርቶች ወደ አፍሪካ ሲገቡ ኢትዮጵያ አንዷ መዳረሻቸው ነበረች፤ በተጨማሪም የቻይና ኤክሰፐርቶች በቪዲዮ በመታገዝ የልምድ ልውውጥና እርስ በእርስ መማማር አድርገዋል፡፡

የቻይና ኩባንያዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በሚደረገው ትግል የላቀ ሚና ያለውን የመመርመሪያ ኪት ማምረቻ ፋብሪካ በኢትዮጵያ በመገንባት ወደ ስራ አስገብተዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ ሁለቱ አገራት ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ድጋፍ ለመስጠትና ለመርዳት በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

አፍሪካ ኮቪድን ለመከላከል ለምታደርገው ጥረት ቁልፍ ሚና እየተጫወቱም ነው፤ ይኽው ጉዳይ ቻይናና አፍሪካ ኮቪድ-19ን ለመከላከል በትብብር እየሰሩ ለመሆናቸው ሁነኛ ምስክር ነው፡፡

ኢትዮጵያ አገር በቀል ኢኮኖሚ ለመገንባት ጥረት እያደረገች ሲሆን "ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት" በሚል የ10 ዓመት የኢኮኖሚ ልማት ዕቅድ አውጥታ ወደ ስራ ገብታለች፡፡

ሁለቱ አገራት በልማትና ዘርፈ ብዙ በሆነ የትብብር መስክ የሚያስመሰግን ተግባር እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡

ወደ አዲስ ምዕራፍ በመሸጋገር የቻይና-አፍሪካ የትብብር ፎረም ውጤታማ እንዲሆን፤ የቤልት ኤንድ ሮድ ትብብር እንዲጠናከር በጋራ እየሰሩ ነው፡፡

በሌሎች ዘርፎችም ጠንካራ አጋርነት እየታየ ሲሆን የከፍተኛ አመራሮችን ትስስርና ለትብብር የሚያግዙ ስትራቴጂካዊ ፕላኖችን በማጠናከር የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማሳደግ የሚረዱ ከፍ ያሉ እቅዶችን ማዘጋጀት መቻላቸው ይጠቀሳል፡፡

ለትብብሩ መሰረት ሊሆኑ የሚችሉና አጋርነቱን ወደፊት የሚያራመዱ እምቅ አቅሞችን በመለየት በመሰረተ ልማትና በኢንዱስትሪ ዞን ግንባታ፣ በዘመናዊ ግብርና፣ በኢኖቬሽንና ቴክኖለጂ፣ በቱሪዝምና በኃይል ማመንጫ ልማት አብሮ በመስራት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ በጋራ እየሰሩ ነው፡፡

ይህን በመከወን የሁለቱን አገራት ትብብር ወደተሻለ ምዕራፍ በማሸጋገር በቻይና አፍሪካ የሮድ ኤንድ ቤልት ትብብር ሁነኛ ምሳሌ ማድረግ ይቻላል፡፡

የሕዝብ ለሕዝብ ትብብር ትስስሩን በጤና፣ በባህል፣ በትምህርትና በቱሪዝም ዘርፍ እውን በማድረግ የሁለቱን አገራት ወዳጅነት በተመለከተ የአገራቱ ሕዝቦች ከፍ ያለ ድጋፍ እንዲሰጡት ማድረግ ይቻላል፡፡

በዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ጉዳዮች ላይ አጋርነትና አብሮነትን በማስፋት የተባበሩት መንግስታትን ማዕከላዊ መርሆዎች እውን ማድረግ ይቻላል፡፡

መሰረታዊ እውነታዎች ዓለም አቀፍ ግንኙነትን ይቆጣጠራሉ፣ አብሮነትን፣ ፍትሃዊነትንና ሁሉንም በእኩል ዓይን መመልከትን እውን በማድረግ ዓለም አቀፍ ፈተናዎችን በጋራ መጣል ያስችላሉ፡፡

ግማሽ ምዕተ ዓመት ያስቆጠረው የኢትዮጵያና የቻይና ግንኙነት አዲስና ታሪካዊ የእድገት እድሎችን ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ ሁለቱ አገራት በሁሉም ዘርፍ ያላቸውን አጋርነት ወደላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር እየሰሩ ሲሆን በሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ የትብብር አጋርነት በመደገፍ የላቀ ስኬት ለማስመዝገብ ያለመታከት እየተጉ ነው፡፡

በዚህም ለሁለቱ አገራትና ለሕዝቦቻቸው ብሩህ መጻዒ ጊዜን ለመፍጠር አልመዋል፡፡

.

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም