ህወሃት መሰረተ ልማቶችን በማፈራረስ ለትውልድ የማያስብ ጨካኝነቱን አስመስክሯል...በአሶሳ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች

69

አሶሳ፤ህዳር 15/2013(ኢዜአ) በትግራይ ክልል የመሰረተ ልማቶችን እያወደመ የሚገኘው የህወሃት የጥፋት ቡድን ለህዝብ ደንታ የሌለው ጨካኝ መሆኑን በግልጽ እንደሚያሳይ በአሶሳ የሚኖሩ ኢዜአ ያነጋገራቸው የትግራይ ተወላጆች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ በትግራይ ክልል ነጻ በወጡ አካባቢዎች አዲስ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ለሚያከናውነው የመልሶ ማልማት ስራ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡም ተናግረዋል።

በአሶሳ ከ20 ዓመት በላይ የኖሩት የትግራይ ተወላጅ ወይዘሮ ለተሚካኤል ግርማይ እንዳሉት በትግራይ ህወሃት በፈጸመው የመሠረተ ልማት ውድመት ክፉኛ አዝነዋል፡፡

የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች እንዳለው የገለጹት አስተያየት ሰጪዋ፤ “በተለይም የትግራይ ህዝብ ከሌላው ማህበረሰብ የሚገናኝበት ዋነኛ መንገድ ነው” ብለዋል፡፡

ቡድኑ እያወደማቸው የሚገኙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ከፍተኛ በጀት እና ዓመታትን ሊፈጅ እንደሚችል በቁጭት የሚናገሩት ደግሞ አቶ ስዩም ወርቄ የተባሉ ናቸው፡፡

አቶ ተካበ ታደሰ በበኩላቸው “ህወሃት ለሃገር፣ ለወገንም ሆነ ለማንም ያማያስብ ራሱን ብቻ የሚወድ ጨካኝ ቡድን ነው” ብለዋል፡፡

ጁንታው “እወክለዋለሁ” ለሚለው የትግራይ ህዝብ እና የዓለም ቅርስ ለሆነው የአክሱም ሃውልት ከብር ሳይሰጥ የአውሮፕላን ማረፊያውን በከፍተኛ ደረጃ ማውደሙ የሚወገዝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ህወሃት ለመጪው ትውልድ የማያስብ መሆኑን ጭምር ይኸው የጥፋት ድርጊቱ በግልጽ እንዳሳየም አቶ ተካበ በቁጭት ገልጸዋል።

በክልሉ በአዲስ መልክ የተዋቀረው የክልሉ ጊዜያዊ መንግስት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የክልሉ ነዋሪዎች ቅድሚያ የሚሰጥ መሆን እንዳለበት ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡

የትግራይ ህዝብ ከራሱ አልፎ ሃገርን ለመለወጥ በስራ የሚተጋ እንደሆነ ገልጸው፤ የክልሉ ባለሃብቶችም በነጻነት የሚሠሩበት ሁኔታ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ሊመቻች እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

ከጁንታው አፈና በወጡ የትግራይ አካባቢዎች የሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር በቡድኑ ጥፋት የተጎዱትን ለመርዳት እና ስነ-ልቦናቸውን ለማደስ ይሠራል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡

መላው የትግራይ ህዝብም ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጎን መቆም እንዳለበት ነዋሪዎቹ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም