በትግራይ ህግ ለማስከበር የተጀመረው ወሳኝ ተልዕኮ እንዲሳካ የክልሉ ህዝብ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

79

ድሬዳዋ፣ ህዳር 15/2013(ኢዜአ) ህግ ለማስከበር የተጀመረው ወሳኝ ተልዕኮ ፈጥኖ እንዲሳካ የክልሉ ህዝብ አዲስ ከተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ መንግስት ጋር በመተባበር የድርሻውን እንዲወጣ በድሬዳዋ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ጥሪ አቀረቡ። 

ተወላጆቹ ከኢዜአ ጋር በወቅታዊ የሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ባደረጉት ቆይታ በክልሉ መንግስት ህግን ለማስከበር እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል ምሁራን በየደረጃው ለሚገኘው ህዝብ እውነትን በማሳወቅ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ለማጠናከር መስራት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

ከተወላጆቹ መካከል አቶ ሰናይ ሲሳይ በሰጡት አስተያየት ክልሉን እያፈረሰ የሚገኘው የህወሃት ጁንታ በሀገሪቱ ታሪክ ተፈፅሞ የማያውቅ ወንጀል በመስራቱ  በህግ ሊጠየቅ  ይገባል ነው ያሉት።

መንግስትና የሀገር መከላከያ ሠራዊት የጀመሩት የህግ የበላይነት የማረጋገጥ የመጨረሻ ምዕራፍ በስኬት እንዲጠናቀቅ  የክልሉ ህዝብ ኃላፊነቱን ሊወጣና ሊረባረብ ይገባል ብለዋል፡፡

አዲስ ከተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ  አስተዳደር ጋር በመተባበር የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

ከህግ ማስከበሩ በተጓዳኝ የህወሃት ጁንታ በክልሉ ያወደመውን መሰረተ ልማትና የተሰደደውን ህዝብ በፍጥነት ወደ ነበረበት ለመመለስ ከተቋቋመው አስተዳደር  ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ዕቁበማርያም በሪሁን ናቸው፡፡

በድሬዳዋ የሚገኘው ትግራዋይ ከሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር በመተባበር ድጋፍ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡  

ወጣት ህይወት ገብረእየሱስ በበኩሏ በተለይ የክልሉ ምሁራን በዚህ ታሪካዊ ወቅት ህግ የማስከበሩን ዘመቻ መደገፍና ያለፍላጎቱ ተታሎ ህይወቱን እየሰጠ የሚገኘውን ወጣት መታደግ፣ ልዩ ኃይልና ሚሊሻዎች በመንግስት የተሰጣቸውን ዕድል እንዲጠቀሙ በአደባባይ ማስተማር ይጠበቅባቸዋል ብላለች ፡፡

ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወደ ቤታቸው ለመመለስ የሚደረገው ጥረት መጠናከር እንዳለበትም ተናግራለች፡፡

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከፌደራልና ከሌሎች ክልሎች እንዲሁም በመላው ሀገሪቱ ከሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ጋር በመነጋገር ጁንታው የፈጠረው ችግር በፍጥነት እንዲስተካከል ተቀናጅተው  መስራት እንዳለባቸውም አመልክታለች፡፡

አቶ ኃይለማርያም ተክሌ  በ21ኛው ክፍለ ዘመን መሆን የሌለበት ጥፋት በህወሃት ጁንታ መፈጸሙን በማውገዝ፤ ህግ ለማስከበር በመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የሚገኘው ዘመቻ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ሁላችንም አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል፡፡

 በጊዜያዊነት የተቋቋመው የክልሉ መንግስት ነፃ በወጡ አካባቢዎች ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ዘላቂ ሰላምና በጋራ የማልማትን ጥቅሞች ያነገቡ አደረጃጀቶችና አሰራሮችን ዘርግቶ መስራት እንደሚገባ የተናገሩት አቶ ቴዎድሮስ ተስፋዬ፤ እኛም ከያለንበት ስፍራ አስፈላጊው ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

ህግ የማስከበሩ ተልዕኮ በፍጥነት እንዲሳካ ተደብቀውና ድምፃቸውን አጥፍተው የሚገኙት የክልሉ ምሁራን በአደባባይ ወጥተው ህዝቡ ከሠራዊቱ ጎን እንዲቆም በመቀስቀስና ንፁሃንን ካለአስፈላጊ ስደትና መስዋዕትነት ለመታደግ ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ወጣት ኤፍሬም ካህሳይ በበኩሉ በድሬዳዋ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ከሌሎች እህት ወንድሞቹ ጋር በመደራጀት የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ በአስተማማኝ መንገድ እየጠበቁ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ለመከላከያ ሠራዊት ተልዕኮ መሳካት በድሬዳዋ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ደም በመለገስና ከደመወዛቸው 20 በመቶ በማዋጣት የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጿል፡፡

ወጣት ብርክቲ ገብረማርያም የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ወደ ክልሉ በመውረድ የትግራይ ህዝብ ስለብልጽግና የተሰበከውን የተሳሳተ መረጃን  በፍጥነት የማስተካከልና ተባባሪ እንዲሆን መስራት እንዳለበት ተናግራለች፡፡

የጁንታ ቡድን በተሰጠው ጊዜ ገደብ እጁን በመስጠት በክልሉ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ሰብአዊና ቁሳዊ ጥፋቶች እንዲያስቀር ተወላጆቹ  መልዕክታቸውን  አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም