የመንገድ ፕሮጀክቶች የአፈጻፀም ውስንነትና የጥራት ችግሮች ሊታረሙ ይገባል - የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

64

አዲስ አበባ ህዳር 14/2013 (ኢዜአ) በአብዛኞቹ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች የሚታዩ የአፈጻፀም ውስንነትና የጥራት መጓደል ችግሮች እንዲታረሙ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ። 

የምክር ቤቱ የግብርና፣ አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንን የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የስራ አፈፃፀም ገምግሟል።

አብዛኞቹ የመንገድ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እንደማይጠናቀቁና የጥራት ችግር እንደሚስተዋልባቸውም ገልጿል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አልማዝ መሰለ ከመንገድ ልማት ፕሮጀክቶች ዋነኛ ችግሮች መካከል የጥራት መጓደል አንደኛው እንደሆነ ጠቅሰዋል። 

መንገዶች በተገነቡ በአጭር ጊዜ የመፈራረስ ዕድል እየገጠማቸው መሆኑ ለጥራት ችግሩ ማሳያ በመሆኑ ሊታይ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶችም ለረጅም ጊዜ በመጓተታቸው ሳቢያ የሚጠናቀቁበትን ጊዜ እንኳን በአግባቡ ለመረዳት እንደሚያዳግት ነው ያነሱት።

በመሆኑም በነባር መንገዶች ማጠናከርና ማሻሻል እንዲሁም በአዳዲስ መንገዶች ግንባታ የሚስተዋለውን የአፈፀፀም ውስንነት ለማረም በትኩረት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ባለስልጣኑ ፍትሐዊ የመንገድ መሰረተ ልማት እንዲኖር መስራት እንዳለበትና በተለይም የአርብቶ አደር አካባቢዎች መንገዶች በብዛትም በጥራትም ረገድ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ ለመንገድ ፕሮጀክቶች መጓተት ምክንያቶች ናቸው ያሏቸውን የወሰን ማስከበር፣ የካሳ ክፍያ መዘግየትና የፀጥታ ችግሮች ጠቅሰዋል።

የውጭ ምንዛሬና የሲሚንቶ እጥረት፣ ተቋራጮችን መንገድ ገንብተው ካጠናቀቁ ከአንድ ዓመት በኋላ ተጠያቂ የሚያደርግ አሰራር አለመኖርም ለጥራት ችግሮች ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።

ይሁንና በአሁኑ ወቅት የሚገነቡ መንገዶች ከዲዛይን ጀምሮ ጥራትና ጊዜ ታሳቢ ሆነው እንዲሰሩ የሚያደርግ አሰራር መዘርጋቱን ገልፀዋል።

በዚህም የመንገድ ግንባታ የሚያጓትቱ ተቋማትን የማገድ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም