የደቅ ደሴት ነዋሪዎች የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆኑ

62
ባህር ዳር ግንቦት 5/2010 በባህር ዳር ዙሪያ ጣና ሃይቅ ውስጥ በምትገኘው የደቅ ደሴት ነዋሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በፀሐይ ኃይል የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ መብራት አገልግሎት ተጠቃሚ ሆኑ፡፡ ሶስት ሚሊዮን 500ሺህ ብር በሆነ ወጪ  የተተከለው በፀሐይ ኃይል የሚሰራው የኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት ትናንት ተመርቋል። የአማራ ክልል ውሃ መስኖና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብርሃም መንገሻ በፕሮጀክቱ ምረቃ ወቅት እንደገለጹት የደቅ ደሴት በጣና ሃይቅ የተከበበ በመሆኑ ነዋሪዎች ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር  ለማገናኘት አስቸጋሪ ሆኖ ህብረተሰቡ ለዘመናት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ሳይሆን ቆይቷል። መንግስት ችግሩን በመረዳት ከሬንሲስ ኢንጂነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጋር በመተባበር ባቋቋመው ፕሮጀክት ከ200 በላይ አባወራዎች የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ መብራት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ 18 ነጥብ 42 ኪሎ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው ጠቁመው ብርሃን ለመስጠት ብቻ ሳይሆን ኑሮን ለማሻሻል የሚያስችሉ ስራዎችን ማከናወን እንዲቻል ተደርጎ የተሰራ መሆኑም ገልፀዋል። ህብረተሰቡ አጠቃቀሙን እስኪለምደው ድረስ  እስከ ሦስት ዓመት  የግል ማህበሩ የሚያስተዳድረው ይሆናል ፤ የእውቀት ሽግግር ካደረገ በኋላ  ለመንግስት ያስረክባል። በጣና ሀይቅ  በመከበባቸው  ምክንያት  ለመደበኛ የኤሌክትሪክ መስመር ተደራሽ ባለመሆናቸው ሲቸገሩ መቆየታቸውን የተናገሩት ደግሞ የደቅ ደሴት ነዋሪ  አቶ ብሩክ ካንተይገኝ ናቸው። የኤሌክትሪክ መብራት ከገባላቸው ወዲህ አዲስ ህይወት መኖር እንደጀመሩ አመልክተዋል። "መብራት አገኛለሁ የሚል አስቤውም አላውቅም  ምክንያቱም በጣና ተከበን የምንገኝ ህዝቦች በመሆናችን ነው" ያሉት  አቶ ብሩክ ህብረተሰቡን ከኩራዝ መብራት ከማላቀቁም በተጨማሪ  ፍሬጂ፣ቴሌቪዥና ሌሎች ዘመናዊ መገልገያዎችን ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው ገልጸዋል። ወጣት ቀረባት ታድጌ በበኩሏ በፀሐይ ኃይል የሚሰራ  ኤሌክትሪክ  አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸው የዘመናት ጥያቄያቸው ምላሽ ያገኘና የነበረባቸው ችግር መፈታቱ ተናግራለች፡፡ መምህር እስጢፋኖስ እውነቱ በሰጡት አስተያየት በአካባቢው የኤሌክትሪክ መብራት አገልግሎት ለማግኘት በግላቸው ጀኔረተር ገዝተው ይጠቀሙ እንደነበርበና በዚህም ለከፍተኛ ወጪ ተዳርገው መቆየታቸውን አውስተዋል። በፕሮጀክቱ ምረቃ ስነ-ስርዓት ወቅት የመንግስት ስራ ኃላፊዎች ፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም