ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቤተክርስቲያን አባቶች መካከል እርቅ ለመፍጠር የሚሰራው ልዑክ በትዕግስትና በአስተዋይነት እንዲሰራ መከሩ

66
አዲስ አበባ ሀምሌ 11/2010 በአገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች ጋር እርቅ ለመፍጠር የሚሰራው ልዑክ በትዕግስትና በአስተዋይነት ተልዕኮውን እንዲያከናውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መከሩ። በሁለቱ ወገኖች መካከል ሰላም ለማውረድ ከ16 ወራት በፊት የተቋቋመው የእርቀ-ሰላም አስተባባሪ ልዑክ የመጨረሻ ጉዞውን ወደ አሜሪካ ያደርጋል። ልዑካኑን በጽህፈት ቤታቸው ያሰናበቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ልዑካኑ እርቀ-ሰላም ማውረድ ፈታኝ ተግባር መሆኑን በመገንዘብ ስራቸውን በትዕግስትና በአስተዋይነት እንዲያከናውኑ መክረዋል። በሁለቱ ወገኖች መካከል የተፈጠረውን ልዩነት በእርቀ-ሰላም በመፍታት ቤተክርስቲያኗን ጠንካራ ተቋም ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሃብት እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤተክርስቲያኗን ወደአንድ መመለስ ከምንም ስራ በላይ እንደሆነም አመልክተዋል። የሃይማኖቱ ተከታይ ያልሆኑ ሰዎችም ጭምር ከሃይማኖት ማግኘት የሚገባቸውን ደስታ እያጡ በመሆኑ በሁለቱ መካከል የተፈጠረው ግንብ ፈርሶ ወደ አንድ መምጣት አስፈላጊና ወሳኝ" መሆኑን ለልዑካኑ ገልጸዋል። መንግስት እርቀ-ሰላም እንዲወርድ የሚጠበቅበትን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም