የአፋር ወጣት በተፈጥሮ ሃብቱ እንዳይጠቀም ያደረገውን ቡድን የጥፋት ሴራ ነቅቶ መጠበቅ አለበት- አቶ አወል አርባ

126

ሰመራ፣ ህዳር 13/2013( ኢዜአ )  የአፋር ወጣት በተፈጥሮ ሃብቱ የበይ ተመልካች አድርጎ ላቆየው የህወሃት ቡድን የጥፋት ሴራ መጠቀሚያ ላለመሆን ተገቢውን ጥንቃቄና ክትትል ሊያደርግ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳደር አቶ አወል አርባ አሳሰቡ ።

የክልሉ መንግስት የወጣቱን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎችን በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ርእሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

የማሄዲፉ ጨዉ ግብይት ሃላፊነቱ የተወሰነ አክሲዮን ማህበር ጉባኤ ላይ የተገኙት ርእሰ-መስተዳድሩ እንደተናገሩት ሃገራዊ ለውጡን ተከትሎ የክልሉ መንግስት የወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ነው።

"በተለይም በአፍዴራ ጨዉ ዙሪያ ከዚህ በፊት የነበሩ የአሰራር ግድፈቶችን በማረም ለዘመናት ህብረተሰቡን ያገለለውን አሰራር በማረም የአካባቢውን ወጣቶች ወደ ስራ ለማስገባት ተችሏል" ብለዋል።

"በተጨማሪም ከፋብሪካ በአዮዲን ተቀነባብሮ የሚወጣ ጨዉ አከፋፋይነት ላይም ወጣቶች ተደራጅተዉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ክልሉ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ነው"ብለዋል።

"የማሂዲፉ ጨው ግብይት አክሲዮን ማህበርም የዚሁ ጥረታችን ማሳያ ሲሆን ማህበሩ በሂደት ጎልብቶ ወጥቶ ጠንካራና ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማስቻል የክልሉ መንግስት ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

ከክልሉ መንግስት ድጋፍ በተጎዳኝ ለማህበሩ ስኬት ወጣት የማህበሩ አባላት ሚና ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ-መስተዳደሩ ወጣቶቹ ባገኙት አጋጣሚዎች ተጠቅመው እራሳቸውን ከአልባሌ ተግባር በማራቅ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

"ለዚህም የሚሆን የመስሪያ ቦታ፣ የብድር አቅርቦትና ተያያዥ ምቹ የአሰራር ስርአቶችን የክልሉ መንግስት አመቻችቷል"ብለዋል።

ሰርቶ መለወጥም ሆነ ማደግ የሚቻለዉ ሠላምና መረጋጋት ሲኖር በመሆኑ ወጣቶች ለአካባቢያቸዉ ሠላም ከመቼውም በላይ ተግተዉ ሊሠሩ እንደሚገባቸውም አመልክተዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች የህዋሃት ሴራ ቢሆንም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የየአካባቢውን ህብረተሠብ መጠቀሚያ እንደሚያደርጉ ጠቁመው የክልሉ ወጣቶች እንደ እስከ ዛሬው ሁሉ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።

የማህበሩ ሊቀመንበር ወጣት ከድር ሃንፈሬ ከተመሠረተ ዘጠኝ ወራት ብቻ የሆነዉ ማህበሩ ከ1 ሺህ 800 በላይ አባላትን አቅፎ የያዘ መሆኑን ተናግሯል።

ከክልሉ መንግስት ባገኘዉ ድጋፍ ማህበሩ እስከ 75ሺህ ኩንታል ጨዉ ከፋብሪካ አዉጥቶ በማከፋፈል የአባላቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አበረታች ጅምር ላይ እንደሚገኝም አብራርቷል።

የጀመሩት የስራ እንቅስቃሴ ተጠቃሚነት በዘላቂነት እንዲቀጥል የሃገር ሰላም አስፈላጊ መሆኑን የገለጸው ወጣቱ ህግን የማስከበር ዘመቻ ላይ ለሚገኘው የሃገር መከላከያ ሰራዊት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን ገልጿል።

ሌላዉ የማህበሩ አባል አቶ ኡመር ያሲን በበኩሉ "እንደ ወጣት ሰርተን መለወጥ የምንችለዉ የህግ የበላይነትና ሠላም ሲኖር ነው" ብሏል።

"የአካባቢውን ሠላም ከመጠበቅ አልፎ ለዘመናት የአፋር ህዝብ ሲያነሳው ለነበረው የተፈጥሮ ሃብቱ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ መልስ የሰጠ ሀገራዊ ለውጥን ለመቀልበስ የሚደረግ ሙከራን ከመንግስት ጎን በመቆም እታገላለሁ” ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም