በአንድ ሳምንት ውስጥ 51.9 ሚሊዮን ብር የሚገመት የኮንትሮባንድ ዕቃ በቁጥጥር ስር ዋለ

64

ህዳር 13/2013 (ኢዜአ) በአንድ ሳምንት ብቻ 51 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የሚገመት የኮንትሮባንድ ዕቃ በቁጥጥር ስር መዋሉን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።

የተያዙት የገቢና የወጪ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሲሆን ይህም ጨ ከህዳር6-10/2013 ዓ.ም ባሉት ቀናት ነው ተብሏል፡፡

ከዚህ ውስጥ 31,093,012.4 ብር የሚገመተው ወደ ሀገር ሲገባ ሲሆን 20,830,335 ብር የሚሆነው ደግሞ ከሀገር ለማስወጣት ሲሞከር በቁጥጥር የዋለ ነው፡፡

በቁጥጥር ስር የዋሉት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች የቁም እንስሳት፣ የምግብ ምርቶች፣ ጌጣጌጥ፣ አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ እና አደንዛዥ ዕፅ እንደሚገኙበት ተገልጿል።

በከፍተኛ መጠን ከተያዙ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ውስጥ በሞያሌ ቅርንጫፍ ስር በሚገኙ ሞያሌ፣ ያቤሎ፣ ነጌሌ ቦረና፣ ቡሌሆራ መስመር የተያዘ 19,701,775 ብር አሺሽ ተብሎ የሚጠራ አድንዛዥ ዕፅ፣ በሀዋሳ ቅርንጫፍ ስር በሚገኙ ጢጢቻ፣ ጪጩ፣ ኮንሶ፣አዳባ፣ ዲላ መስመር 9,122,370 ብር የሚገመት የተለያዩ አልባሳት ኤሌክትሮኒክስ፣ ሲጋራ፣ ኮስሞቲክስ፣ ልባሽ ጨርቅ፣ መለዋወጫ ተጠቅሰዋል።

በሞያሌ ቅርንጫፍ 6,638,463 ብር የሚገመት የተለያዩ አልባሳት፣ የምግብ ምርቶች፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ሲጋራ፣ ኮስሞቲክስ፣ ልባሽ ጨርቅ፣ መለዋወጫ እንዲሁም በድሬደዋ ቅርንጫፍ ሀረር፤ ድሬደዋ፣ ለጋር፣ ቢዮቆቤና ደወሌ መስመር 3,206,200 ብር የሚገመት የተለያዩ አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ሲጋራ፣ ኮስሞቲክስ፣ ልባሽ ጨርቅ፣ መለዋወጫ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ነው የተገለጸው፡፡

እንዲሁም በባህርዳር ቅርንጫፍ ሰራቫ፣ ሻውራ፣ መተማ የመቆጣጠሪያ ጣቢያዎች 30 የብሬይን ጥይት፣ 166 የክላሽ ጥይት፣ 2771 የአሜሪካን ዶለር በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል፡፡

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ አስራ ሁለት የጉምሩክ ኮሚሽን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የተገለፀው መጠን የኮንትሮባንድ ዕቃ በቁጥጥር ስር ለማዋል ፍተሻ፣ ስካንንግ ማሽን በመጠቀም፣ በተሸከርካሪ በመከታተል (በረራ) እና ተከማችቶ የሚገኙበት ቦታ ክትትል በማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል ነው የተባለው፡፡

በተጨማሪም ከክልል ፖሊስ፣ ፌደራል ፖሊስ፣ አድማ ብተና መከላከያ እና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ተቋማት በቅንጅት በተሰራ ስራ በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉ ተጠቁሟል፡፡

ለህገ-ወጦች የፋይናንስ ምንጭ የሚሆነውን የኮንትሮባንድ ንግድ በመግታት ሁሉም ከተባበረ የሀገር ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ እንደሚቻል ሚኒስቴሩ በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም