በአማራ ክልል 3 ሺህ 470 ኪሎ ሜትር መንገዶች ግንባታና የጥገና ተደርጓል

77
ባህርዳርሀምሌ11/2010 በአማራ ክልል በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 3 ሺህ 470 ኪሎ ሜትር ነባርና አዲስ መንገዶች ግንባታና ጥገና  ማከናወኑን የክልሉ ገጠር መንገዶች ኮንስትርክሽን ኤጀንሲ ገለጸ። የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌትነት ዘውዱ ለኢዜአ እንደገለጹት የክልሉን የመንገድ ተደራሽነት ለማሳደግና የተገነቡ ነባር መንገዶችን ደህንነት ለመጠበቅ ኤጀንሲው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው። ከዚህም ውስጥ የክልሉ መንግስት በመደበው በጀት በ38 መስመሮች 312 ኪሎ ሜትር የአዳዲስ መንገዶች ግንባታና ደረጃ ማሳደግ ስራ ተከናውኗል። ቀሪው 3ሺህ 159 ኪሎ ሜትር ነባር መንገዶችን ደግሞ የፌደራል መንገድ ፈንድ ጽህፈት ቤት በመደበው በጀት የጥገና ስራ የተከናወነላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ጥገና ከተደረገላቸው ነባር መንገዶች መካከልም 707 ኪሎ ሜትሩ በወቅታዊ፣ ቀሪው መደበኛ ጥገና የተደረገለት ነው። ጥገና ከተካሄደላቸው ውስጥም ከማክሰኝት - አርብ ገበያ፣ ከቡሶ - ሳይንት፣ ከንፋስ መውጫ - አርብ ገበያ ተጠቃሾች መሆናቸውን አመልክተዋል። አዲስ የተገነባው መንገድ  ደግሞ ቀበሌን ጨምሮ ወረዳን ከወረዳና አነስተኛ የገጠር ከተሞችን እርስ በርስ በማገናኘት የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ማቃለል አስችሏል።   ለመንገዶቹ ግንባታና ጥገና ስራ ከክልሉና ከፌዴራል መንግስት የተመደበ ከ791 ሚሊዮን ብር በላይ በጀትም ጥቅም ላይ መዋሉን አስረድተዋል። በምዕራብ ጎጃም ዞን ደንበጫ ወረዳ የዘለቃ ቀበሌ ነዋሪ  አርሶ አደር ተመስገን የሻነህ በሰጡት አስተያየት ከዋድ ኢየሱስ ዘለቃ የሚወስደው  መንገድ በፊት በመበላሸቱ ምርታቸውን ለገበያ ለማቅረብ ሲቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ዘንድሮ የመንገዱ ደረጃ አድጎ በመገንባቱ ማዳበሪያ በወቅቱ ቀበሌያቸው ድረስ እንዲቀርብና ምርትም በቀላሉ ለገበያ ለማቅረብ እንዳገዛቸው ገልፀዋል፡፡ በመንገዱ መበላሸት ምክንያት ወደ ቀበሌው ለመግባት ይቸገሩ የነበሩ አምቡላንሶችም አሁን በቀላሉ ገብተው ነፍሰ-ጡር እናቶችን ወደ ጤና ተቋማት በማድረስ ላይ መሆናቸውን መመልከታቸውን ገልፀዋል፡፡ ኤጀንሲው ባለፈው ዓመትም በክልሉ ከ627 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጭ 3 ሺህ 345 ኪሎ ሜትር የአዲስ መንገዶች ግንባታና ጥገና ስራ ማከናወኑ ታውቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም