በአሜሪካ ከሚኖሩ ብጹዓን አባቶች ጋር እየተደረገ ያለው የእርቀ ሰላም ሂደት ቀጥሏል

79
አዲስ አበባ ሀምሌ11/2010 በአሜሪካ አገር ከሚኖሩ ብጹዓን አባቶች ጋር እየተደረገ ያለው የእርቀ ሰላም ሂደት እንዲሳካ ጥረት እያደረገች መሆኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ገለጸች። ቤተ ክርስቲያኒቱ የሰላም እርቁን የሚያስተባብሩ ልዑካን አባላትን ወደ አሜሪካ መሸኘቷን በላከችው መግለጫ አስታውቃለች። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓርትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በአባቶች መካከል መከፋፈል ከመፈጠሩ በፊት የነበረውን ሰላምና አንድነት አስታውሰውዋል። "ሰላምና ፍቅር ለሁሉም ጥሩ ነው" ያሉት ብጹዕነታቸው፤ ያለፈውን ሁሉ ረስተን ወደ ጥንት አንድነታችን እና ወደ ጥንት ፍቅር ፣ ወደ ጥንት ህይወታችን እንድንመለስ እግዚአብሔር ይርዳን  በማለት ምኞታቸውን ገልጸዋል። "ሰላም በእጃችን ሳለች አትታወቅም፤ ከእጃችን ከወጣች በኋላ እንጂ፤  ቤተክርስቲያን የሰላም ቤትና ምንጭ ናት፤ በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን የመለያየትና የመከፋፈል ምክንያት አይደለችም" ብለዋል። የቤተክርስቲያን ስራ ሰላም ፍቅርና አንድነት መመስረት ሆኖ አገርን መጠበቅ፣ ትምህርት ማስተማር ነው በመሆኑም የቤተክርስቲያን አገልጋይ አባቶች ካህናትና ምዕመናን ለሰላም፣ ለፍቅርና ለአንድነት እንዲሰሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። የእርቀ ሰላም ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው የተጀመረውን እርቀ ሰላም ዳር ለማድረስና እውን ለማድረግ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ የእረቀ ሰላም ሂደት እውን ሆኖ የቤተክርስቲያን ሰላምና የአባቶችን አንድነት ለማየት የቤተክርቲያኗ ጸሎትና ድጋፍ እንዳይለያቸውም ጠይቀዋል። የኮሚቴ አባላቱ ላቀረቡት የእረቀ ሰላም ጥያቄ ከቅዱስ ፓትርያርኩና ከቅዱስ ሲኖዶስ ላገኙት አዎንታዊ ምላሽና ቀና ትብብርም ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ካነገቧቸው ተግባራት መካከል  በኃይማኖቶች መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ማስታረቅና አንድነት መፍጠር አንዱ መሆኑ ይታወቃል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም