የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት አሰራሩን ሙሉ በሙሉ ከወረቀት ነጻ አደረገ

539
አዲስ አበባ ሃምሌ 11/2010 የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት አሰራሩን ሙሉ በሙሉ ከወረቀት ነጻ አደረገ። የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ለድርጅቱ የሰራውን 'ኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላን' የተሰኘውን ፕሮጀክት ትናንት ምሽት ለድርጅቱ አስረክቧል። ፕሮጀክቱ በአገሪቷ ያሉ የድርጅቱ ቅርጫፎችን በሶፍትዌር መሰረተ ልማት የሚያገናኝ ሲሆን ይህም ከሰው ሀብትና መረጃ አያያዝ ጋር በተያያዘ የሚሰሩ ሥራዎችን ከወረቀት ንክኪ ሙሉ በሙሉ ነጻ የሚያደርግ ነው። በዚሁ መሰረት የድርጅቱ ዘጠኝ ቅርጫፎች የተሳሰሩ ሲሆን ፕሮጀክቱን ወደ ሥራ ለማስገባትም 4 ዓመታትን ፈጅቷል። በኤጀንሲው የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ አንዋር የሱፍ እንደተናገሩት፤ የፕሮጀክቱን ውጤት ለመገምገም በሙከራ ደረጃ ለሁለት ዓመት ያህል ሲተገበር ቆይቷል። በድርጅቱ ውስጥ የንብረት ብክነቶች፣ የነዳጅ ዘይትና ድንጋይ ከሰል የማስገባት ሂደቱ ላይ የሚታዩ መጓተቶችን፣ የሥራ መጠባበቅና ድግግሞሽንና የመረጃ ደህንነት የመሳሰሉ ችግሮች ነበሩ ብለዋል። የተቀናጀ የፋይናንስና የበጀት፣ የሰው ሀብት አስተዳደር፣ የንብረትና የግዥ አስተዳደር፣ የሽያጭ አስተዳደር፣ የላብራቶሪ መረጃ አስተዳደር ሥራዎችና የአቅርቦት ሰንሰለት ሥራዎች በፕሮጀክቱ ሲከናወኑ መቆየቱን ጠቁመዋል። እንደ አስተባባሪው ገለጻ ፕሮጀክቱ የሰራተኞችን የሥራ ቅልጥፍና ከማሻሻሉም ባለፈ የንብረት ብክነትንና የሥራ መንዛዛትን የሚያስቀር፣ ስራዎችን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ የሚያስችልና የመሳሰሉ ውጤቶች ተገኝተውበታል። በተለይ ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች መሰራቱ ደግሞ  አገራዊ አቅም ከመፍጠሩም ባለፈ የውጭ ምንዛሪን ማዳን መቻሉንም አስረድተዋል። አቶ አንዋር እንደሚገልጹት የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ ከ 31 ሚሊዮን 800 ሺህ በላይ ብር ነው። የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለማርያም ድርጅቱ በየወሩ ከ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት እንደሚያካሄድ ገልጸው፣ ፕሮጀክቱ ስኬታማ ሥራ እንዲሰራ እገዛ እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል። ድርጅቱ አሰራሩ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መታገዙ የአገልግሎት ቅልጥፍናውን 90 በመቶ እንዳሻሻለውም ተናግረዋል። በዕለቱ ለፕሮጀክቱ ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉ ባለሙያዎችና አካላት እውቅና ተሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም