ኢትዮጵያና ኳታር በሁለትዮሽ ግንኙነትና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አደረጉ

107
አዲስ አበባ ግንቦት 5/2010 ኢትዮጵያና ኳታር በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት ማጠናከር በሚችሉባቸውና በአካባቢያዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ ትናንት ዶሃ ውስጥ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየው በኳታር ዶሃ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ናቸው። ሚኒስትሩ በዚሁ ጉብኝታቸው ወቅት ከኳታሩ አቻቻው ሼክ ሞሀመድ ቢን አብዱልራህማን አልታኒ ጋር ተገናኝተው በሁለትዮሽና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል። ከቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት በተገኘው መረጃ መሰረት ኳታርና ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ተባብረው በመስራት ላይ ሲሆኑ የኳታር ኤሚር ሼክ ታሚም ቢን ሀማድ አልታኒ  ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገው አንደነበር ይታወሳል። የኳታሩ ኤሚር በዚህ ጉብኝታቸው ሁለቱ አገራት በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዙሪያ በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት የሥራ ኃላፊዎች ጋር መክረዋል። አገሮቹ በልዩ ልዩ መስኮች በትብብር ለመስራት የሚያስችሏቸውን ስምምነቶች እና የመግባቢያ ሰነዶችንም ፈርመዋል። ኢትዮጵያና ኳታር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2008 ዓ.ም መቋረጡ ይታወሳል። ለግንኙነታቸው መቋረጥ ምክንያቱ ደግሞ የኳታር መገናኛ ብዙኃን በተለይም አልጀዚራ አሸባሪ ተብለው የተሰየሙ ድርጅቶችን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እንደሚደግፍ ኢትዮጵያ ይፋ ማድረጓ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት ድርጊቱን በመቃወም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ እንዲቋረጥ አድርጓል። የኳታሩ ኤሚር ሼክ ሀማድ ቢን ካሊፋ አል ታኒ ከሦስት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ያደረጉት ይፋዊ ጉብኝት ግን ሁለቱ አገራት ግንኙነታቸውን ዳግም እንዲያድሱ በር የከፈተ ሆኗል። ይህም በመሆኑ አገሮቹ ተደጋጋሚ ቀረጥ በማስቀረት፣ በአየር ትራንስፖርት፣ በኢንቨስትመንት፣ በባህል እና ንግድ ላይ ተባብረው ለመስራት 11 የመግባቢያ ስምምነቶችን እንድፈራረሙ አስችሏቸዋል። በተመሳሳይ ባለፈው ዓመትም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በኳታር ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርገው ነበር።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም