በሲዳምኛ ቋንቋ በየሳምንቱ የሚታተም ጋዜጣ ዛሬ ተመርቆ ይፋ ተደረገ

104

ሀዋሳ ህዳር 10/2013( ኢዜአ) በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት "ባካልቾ " በሚል በሲዳምኛ ቋንቋ በየሳምንቱ የሚታተም ጋዜጣ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተመርቆ ይፋ ተደረገ።

በምረቃው ሥነ- ሥርዓት  ወቅት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ እንዳሉት ላለፉት 27 ዓመታት በሲዳምኛ ቋንቋ ጋዜጣ ለማሳተም ቢታሰብም አፋኙ የህወሃት ጁንታ  እንዳይሳካ ተጽዕኖ ሲያደርግ ቆይቷል።

በለውጡ መሪ የቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ የሲዳማ ህዝብ የሚፈልገውን መረጃ በቋንቋው ማግኘት እንዲችል ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በመነጋገር የመጀመሪያው የሲዳምኛ ጋዜጣ ለህትመት መብቃቱን ይፋ አደርገዋል።

የክልሉ መንግሰት የመገናኛ ብዙሀን አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ   አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

አምና በዛሬው ዕለት የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ ምላሽ የተገኘበት መሆኑን አስታውሰው በዚህ ዕለት ጋዜጣው ለምረቃ መብቃቱም ቀኑን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

ለጋዜጣው ዕውን መሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣንና ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ዋና ዲይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ በበኩላቸው የንባብ ባህልን ለማዳበር ሁሉም ሰዎች በሚረዱት ቋንቋ መረጃ ማግኘት እንዲችሉ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ለዚህም የሲዳማ ክልል ከተቋቋመ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የጋዜጣ ህትመት ማስጀመሩ አርአያነት እንዳለው  ጠቁመው ሌሎች ክልሎችም ከዚህ ልምድ በመውሰድ የመገናኛ ብዙሀን አማራጮችን ማስፋት እንዳለባቸው ተናገረዋል።

ለዚህም እውን መሆን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ዶክተር ጌታቸው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ  እንዳሉት  80 ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረው ድርጅቱ ለመላው የሀገሪቱ ህዝብ መረጃ እያደረሰ መሆኑንና በርካታ የሀገሪቱን ዕውነታዎች ሰንዶ ለታሪክ አቆይቷል።

ሚዲያ ሀሳብን የመግለጽ የነጻነት ምልክት ነው ያሉት  አቶ ጌትነት በአማርኛ፣ ኦሮሚኛ ፣ ትግርኛና አሁን ደግሞ ሲዳምኛ ቋንቋ በተጨማሪ በቅርቡ በአፋርኛና ሶማልኛ ቋንቋዎች ጋዜጣ ማሳተም እንደሚጀምር አስታውቀዋል።

በሥነ-ሥርዓቱ የክልሉና ፌዴራል ከፍተኛ አመራሮች፣ የፕሬስ ድርጅት ቦርድ አባላት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች  ተገኝተዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም