የእምቦጭ አረምን ከጣና ሐይቅ ለማስወገድ ከተያዘው እቅድ አስካሁን 60 በመቶው ተከናውኗል

102

አዲስ አበባ ህዳር 10/2013 (ኢዜአ) የእምቦጭ አረምን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከጣና ሐይቅ ለማስወገድ ከተቀመጠው እቅድ በ20 ቀናት ብቻ 60 በመቶ መከናወኑን የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብርሃም አዱኛ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በጣና ሐይቅ ላይ የተስፋፋውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ ለአንድ ወር የዘመቻ ስራ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የዘመቻ ስራው ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን ከወሩ ውስጥ በ20 የስራ ቀናት ብቻ ውጤታማ ስራ መከናወን ችሏል ብለዋል።

የእምቦጭ አረሙ በተከሰተባቸው 30 ቀበሌዎች መካከል እስካሁን 17ቱን ሙሉ ለሙ ነፃ ለማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል።

የዘመቻ ስራው ሲጀመር በ4 ሺህ 300 ሔክታር ቦታ ላይ የተስፋፋውን አረም ለማስወገድ በተደረገው ጥረት 60 በመቶውን ከአረሙ ነፃ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የአረሙ ነቀላ ባልተጠናቀቀባቸው 13 ቀበሌዎች እስከ ሕዳር 30 ቀን 2013 ዓ.ም የማስወገድ ስራው የሚከናወን መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የአማራ ክልል የውሃ፣ ኢነርጂና ማዕድን ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ማማሩ አያሌው እንዳሉት አረሙን ለማስወገድ በመንግስት ደረጃ በተካሔደው የቅንጅት ስራ መልካም የሚባሉ ውጤቶች ተገኝተዋል።

የእምቦጭ አረሙን የማስወገድ ሂደት ከሰው ጉልበት በተጨማሪ በማሽንና ትራክተሮች ታግዞ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

በቀጣይም አረሙ ዳግም እንዳያንሰራራ ተከታታይ የዘመቻ ስራዎች እንደሚከናወኑ ጠቅሰው የህዝቡም ተሳትፎ እንዳይለይ ጠይቀዋል።

የተፋሰስ ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዳነች ያሬድ በበኩላቸው በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ለማጥፋትና በዘላቂነት ለመታደግ ስትራቴጂዎች ተቀርፀው እየተሰሩ ነው።

እምቦጭን የማስወገድ ስራ በዘመቻ ብቻ ተሰርቶ የሚቆም ባለመሆኑ ቀጣይ ስራዎችም እንደሚኖሩ ነው የተናገሩት።

የእምቦጭ አረምን ከጣና ሐይቅ በማስወገድ የዘመቻ ስራ ከ260 ሺህ በላይ ሰዎች መሳተፋቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም