ከሀገሪቷ የቆዳ ስፋት 43 በመቶው በአየር ፎቶግራፍ ተሸፍኗል -- የኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት

199

አዲስ አበባ ህዳር 8/ 2013 (ኢዜአ) ከኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት 43 በመቶውን በአየር ፎቶግራፍ መሸፈን እንደተቻለ የኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ገለፀ፡፡ 

የአየር ፎቶግራፍ ሽፋኑ መረጃ በዋናነት ለገጠርና ለከተማ መሬት ምዝገባ፤ ለመንገድ ግንባታ፣ ለከተሞች ማስተር ፕላን፣ ለግድብ፣ ለመስኖና ተፋሰሶች በግብዓትነት ጥቅም ላይ መዋሉን የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቱሉ በሻ ገልፀዋል።

ዶክተር ቱሉ ይህን የገለጹት 21ኛው ዓለም አቀፉ የጂኦግራፊ ኢንፎርሜሽን ሳይንስ ቀን "ጂኦስፓሻል ለብልፅግና" በሚል መሪ ሃሳብ በኢትዮጵያ ለ5ኛ ጊዜ በተከበረበት መርሃ ግብር ነው።

በመድረኩ የጂኦስፓሻል የቀጣይ አስር ዓመት ዕቅድ ይፋ ሆኖ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡

ተቋሙ የአገሪቷን እድገትና ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ በአበይት ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር የገለጹት ዶክተር ቱሉ ለተለያዩ ዘርፎች ግብዓት የሚሆኑ የአየር ፎቶግራፎች፣ የሳተላይት ምስሎችና የምድር መረጃዎች በማሰባሰብ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዋነኝነትም የጂኦስፓሻል መሰረተ ልማቶች ማስፋፋትና ቴክኖሎጂዎችን በማበልፀግ የመረጃ ተደራሽነት ማስፋት ላይ ይሰራል ብለዋል፡፡

በቀጣዮቹ 10 ዓመታት በትኩረት ከሚሰራባቸው ጉዳዮች መካከል በጅማሬ ላይ የሚገኘው የጂኦስፓሻል ኢንዱስትሪ መፍጠር ቀዳሚ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ዘርፉ አዳዲስ የስራ ዕድሎችና የኢኮኖሚ አቅም ከመፍጠር አንፃር የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረውም አክለዋል።

አሁን ያለውን 43 በመቶ የአየር ፎቶግራፍ ሽፋን ወደ 100 ማድረስም የ10 ዓመቱ ዕቅድ አካል መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

የአገሪቷን የዲጂታል ኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጥ ለ73 ከፍተኛና መካከለኛ ከተሞች ዲጂታል የአድራሻ ስርዓት ፕላት ፎርምም ይዘረጋል፡፡

ችግር ፈቺና ፈጠራ የታከለባቸው ምርምሮች መስራት፣ ጥቅም ላይ ማዋልና ብሔራዊና ዓለምአቀፍ ትብብሮችን መፍጠርም እንዲሁ።

የቴክኖሎጂ አቅም ለመፍጠርና ያሉትን በአግባቡ ለመጠቀም እያጋጠመ ያለው እጥረትና ከአገር ውጭ ባለው የጂኦስፓሻል ኢንዱስትሪ ገበያ ለመሳተፍ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖርና መሰል ችግሮችን ለማቃለል ከጉዳዩ ባለቤቶች ጋር የሚሰራበት እንደሆነም አስረድተዋል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኅይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ ኮሚሽነሮችና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በመርሃ ግብሩ ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም