ኢትዮጵያ ሁለተኛዋን ሳተላይት በታህሳስ ወር ወደ ህዋ ለማምጠቅ ተዘጋጅታለች

89

አዲስ አበባ ህዳር 09/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በታሪኳ ሁለተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት በመጭው ታህሳስ ወር ወደ ህዋ ለማምጠቅ መዘጋጀቷን የስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት የ2013 በጀት ዓመት የአንደኛ ሩብ ዕቅድ አፈጻጸምን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ፤ በታህሳስ 2013 ዓ.ም ቀደም ሲል ከመጠቀችው የመሬት ምልከታ ሳተላይት ጋር ተመሳሳይ አገልግሎት የምትሰጥ ተጨማሪ 12 ኪሎ ግራም የምትመዝን ሳተላይት ወደ ህዋ ለማምጠቅ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

ሳተላይቷ በማዕድን፣ ግብርና እና ሌሎች አስፈላጊ ዘርፎች መረጃዎችን የመሰብሰብ አገልግሎት የምትሰጥ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በቻይና ከሚገኝ ኩባንያ ጋር በመተባበር ሳተላይቷ የበለጸገች መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ 5 ነጥብ 4 ሜትር ሪሶሉሽን ያላትና ባለፈው ዓመት ከመጠቀችው "ETRSS-1" የተሻለ ሪሶሉሽን እንዳላት አብራርተዋል።

የመጀመሪዋ ሳተላይት ከመጠቀችበት ጣቢያ ጋር የማገናኘት ሥራ እየተጠናቀቀ መሆኑንም ያመለከቱት አቶ አብዲሳ፤ ሳተላይቷ በኢትዮጵያ ስም በዓለም አቀፉ የቴሌኮሙንኬሽን ህብረት እንድትመዘገብ የማድረግ ሥራ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያ የራሷ የመሬት ምልከታ ሳተላይት እስኪኖራት እየተገነባ ያለው የመሬት መረጃ መቀበያ ጣቢያ አንቴና በሁለተኛው ሩብ አመት ይጠናቀቃል” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አንቴናው ከአምስት የተለያዩ ሳተላይቶች መረጃ የመቀበል አቅም እንዳለው ጠቁመዋል።

“ኢትዮጵያ የቴሌኮሙኒኬሽን ሳተላይት በቀጣዮቹ ሦስትና አራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ እውን ለማድረግ እየሰራች ትገኛለች” ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የቅድመ ዝግጅትና የአዋጭነት ጥናት የተጠናቀቀ ሲሆን ለዕቅዱ መሳካት ከ350 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያስፈልጋል ተብሏል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እምየ ቢተው ኢንስቲትዩቱ ሳተላይቷን ለማምጠቅ እየተከናወነ ያለውን ተግባር የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲከታተልና እንዲደግፍ አሳስበዋል።

“ሚኒስቴሩ በቴክኖሎጂ የዳበረ ማህበረሰብ ለመፍጠር የጀመራቸውን ፕሮጀክቶች ወደ ተግባር ለመቀየር በትኩረት መስራት አለበት” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም