አዲስ አበባን ከሚመጥናት የከተማነት ደረጃ ለማድረስ በአዲስ አስተሳስብና መንፈስ አንደሚሰሩ ተሿሚው ምክትል ከንቲባ ተናገሩ

86
አዲስ አበባ ሀምሌ 10/2010 አዲስ አበባ ከሚመጥናት የከተማነት ደረጃ እንድትደርስና ለነዋሪዎቿ የምትሰጠውን አገልግሎት እንድታማሏ በአዲስ አስተሳስብና መንፈስ እንደሚሰሩ የመዲናዋ አዲሱ ምክትል ከንቲባ ተናገሩ። የአዲስ አበባ ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ በምክትል ከንቲባነት የተሾሙት ኢንጂነር ታከለ ኡማ፤ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ክንውኖች የሚዘወርባት የኢትዮጵያ  ሙሉ ገጽታ ማሳያ ከተማ መሆኗን ገልጸዋል። "በከተማዋ በመንገድ፣ በውሃና ፍሳሽ፣ በቤቶች ግንባታና በሌሎች የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች አበረታች ጅምሮች አሉ" ያሉት አዲሱ ተሿሚ፤ ይህን ከዳር ለማድረስ ቀጣይ ቅንጅታዊ አሰራሮች እንደሚጠይቁ ተናግረዋል። "አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካም ዋና ከተማ ናት" ያሉት ኢንጅነሩ፣ ከተማዋ ለአፍሪካ፣ ለኢትዮጵያና ለኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መዲናነቷን ያሟላችና ነዋሪዎቿ የሚገባቸውን አገልግሎቶች በሚያገኙበት ቁመና ላይ አይደለችም ብለዋል። በመሆኑም አዲስ አበባ ከሚመጥናት የከተማነት ደረጃ እንድትደርስና ለነዋሪዎቿ የምትሰጠውን አገልግሎት እንድታማሏ በአዲስ አስተሳስብና መንፈስ እንደሚሰሩ ነው የገለጹት። በአገልግሎት ተደራሽነትም ሆነ በጥራት ረገድ ብዙ የሚቀራት ከተማ መሆኗን ገልጸው፤  ወጣቶች፣ ባለሀብቶች፣ የሃይማኖት አባቶችና መላው የመዲናዋ ነዋሪዎች ከተማዋን ለመለወጥ በአገሪቷ እየመጣ ካለው የአገር አንድነት ጋር ተደምረው እንዲሰሩ ጠይቀዋል። መዲናዋ ሁሉን አካታችና ዘመናዊ ለማድረግ ብቁና የአገልጋይነት መንፈስ የተላበሰ አመራርና አደረጃጀት እንደሚዘረጉም ምክትል ከንቲባው አረጋግጠዋል። የከተማ አስተዳድሩ ምክር ቤት አባል ባለመሆናቸው በምክትል ከንቲባነት የሚጠሩት ኢንጂነር ታከለ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ታሪክ በምክትል ከንቲባነት የአዲስ አበባ ከንቲባ በመሆን ያገለግላሉ። ከንቲባው የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኬሚካል ምህንድስናና በውሃ አቅርቦትና አካባቢያዊ ምህንድስና የተቀበሉት ኢንጂነር ታከለ፣ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ከተሞችና ቢሮዎች ኃላፊነት ለ11 ዓመታት ማገልገላቸው ተጠቅሷል። የወቅቱ የኦሮሚያ ክልል ትራንስፖረት ቢሮ ኃላፊም ነበሩ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም