ህብረተሰቡ ለአካባቢው ሰላም መረጋገጥ የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ

123
ድሬዳዋ ግንቦት 5/2010 ህብረተሰቡ ከፍትህ አካላት ጋር በመቀናጀት ለአካባቢው ሰላምና ልማት መረጋገጥ  የሚያከናውናቸውን አበረታች ተግባራት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ገለፁ፡፡ ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን ማዕከላቱን መርቀው ሥራ ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት ነዋሪው የአካባቢውን ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ  የሚያደርገው ጥረት አስደሳችና የሚበረታታ ነው፡፡ ህብረተሰቡ ከቤተሰብ ጀምሮ በከተማና በገጠር በማህበረሰብ አቀፍ የፖሊሲንግ አደረጃጀቶች በመታገዝ ከፍትህ አካላት ጋር ተቀናጅተው የሚያከናወኑት አበረታች እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ በድርጅቶችና በህብረተሰቡ ቅንጅት ተገንብተው አገልግሎት የጀመሩት ማዕከላት ነዋሪው ለልማቱና ለሰላሙ መረጋገጥ የሚያደርገው ጥረት ማሳያ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ለግንባታው መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉት አካላት የተዘጋጀውን የምስክር ወረቀትና ልዩ ልዩ ሽልማት የሰጡት የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌታችው አስረስ በበኩላቸው  ማዕከላቱ መገንባታቸው ህብረተሰቡን በሁሉም መስክ ተሳትፎውን እንዲያሳድግና ከፖሊስ ጋር ያለውን ቁርኝት እንዲያጠናክር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልፀዋል፡፡ ማእከላቱ ህብረተሰቡ በትራፊክ አደጋ መከላከል ላይም የድርሻውን እንዲወጣ የሚያግዝ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥፍራ ሆኖም እንደሚያገለግል ገልፀዋል፡፡ የግንባታ ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ አባል አቶ ዜና በየነ ነዋሪውና ድርጅቶች ለማዕከላቱ ግንባታ ህብረተሰቡ በተነሳሽነት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡ ለግንባታዎቹ በጥሬ ገንዘብና በቁሳቁስ ከ820 ሺ ብር በላይ ወጪ  መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ''ህዝቡን በአግባቡ መቀስቀስና ማስተባበር ከተቻለ ነዋሪው ለልማቱ፣ ለሰላሙና ለዕድገቱ ያለውን ሁሉ ለመስጠት ዝግጁ በመሆኑ ይህን ሃብት በአግባቡ ስራ ላይ ማዋል ይገባል''  ያሉት ደግሞ የሀገር ሽማግሌው አቶ ዜና በየነ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም