ለውጡን እንደሚደግፉ በሸኮ እና ጣርማ በር ወረዳዎች ነዋሪዎች ገለጹ

70
ሚዛን/ደብረብርሃን ሀምሌ 10/2010 በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ በመደገፍ የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ የሸኮ እና  የጣርማ በር ወረዳዎች ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ በቤንች ማጂ ዞን የሸኮ ወረዳ ነዋሪ ዶክተር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሰየሙ ወዲህ ላመጡት ሀገራዊ ለውጥ ምስጋና ለማቅረብ ትናንት የድጋፍ ሰልፍ አካሄደዋል፡፡ በወረዳው ማዕከል ሸኮ ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፉ ከተሳተፉት ነዋሪዎች መካከል  አቶ አሪ ጉሩሙ በሰጡት አስተያየት  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ ለሰላምና ለሀገር አንድነት መጠናከር ውጤታማ ስራዎች ማከናወናቸውን ጠቅሰው የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ የሚመክሩ አካላትን በማጋለጥ ለውጡን  እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡ "ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለዘመናት ሳይፈታ የቆየውን ግጭት በቀላሉ መፍታት መቻላቸው አስደስቶኛል "ያሉት ሌላኛው የሰልፉ ተሳታፊ አቶ ዮናስ ዱኩይ ናቸው፡፡ አቶ ዮናስ እንዳሉት  ህዝቡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለውን ድጋፍ በሰልፍ ከመግለጽ ባለፈ በተግባር ማረጋገጥ አለበት፡፡ አቶ ብርሀኑ አያሌው የተባሉ ተሳታፊ በበኩላቸው  የሚፈለገው ለውጥ ከዳር ለማድረስ የዶክተር አብይ አስተሳሰቦችን ተቀብሎ መፈጸም እንደሚገባ ጠቅሰው ሰላም ፣ፍቅርና አንድነትን እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡ የሸኮ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ  አቶ ግዛው ሻሹ ለሰልፈኞቹ ባደረጉት ንግገር "ዶክተር ዓብይ ሀገራችንን የተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚያደርጉትን ጥረት መደገፍ ብቻ ሳይሆን ሁላችንም በተሰማራንበት የሥራ መስክ ውጤታማ በመሆን ለውጡን መደገፍ ይኖርብናል" ብለዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማ በር ወረዳ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት በሀገሪቱ የተጀመረውን   የመደመር አስተሳሰብ እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡ ከወረዳው ነዋሪዎች መካከል የኮሶ በር ቀበሌ አርሶ አደር ደበበ ዓለሙ እንዳሉት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ማጠናከር ይገባል፡፡ " እኔም የእሳቸውን  ምክር በመቀበል መሬቴን  በተሻለ የግብርና ቴክኖለጂ ተጠቅሜ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጠንክሬ በመስራት ለውጡን እደግፋለሁ" ብለዋል፡ ሌላው የአካባቢው ነዋሪ ወይዘሮ የሺ  ብዙወረቅ በበኩላቸው  ጦርነት  የሰውን ልጅ ህይወት ከመቅጠፍም በላይ በተለይ በሴቶች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት እጅግ የከፋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህንን በመገንዘብ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያካሄደችው የሰላም ስምምነት የሚደገፍ መሆኑን ጠቅሰው  "አሁን በአንዳንድ አካባቢዎች  የሚስተዋለው  ፀጥታ ችግር ተገቢነት የለውም "ብለዋል፡፡ በአካባቢያቸው የጥፋት ድርጊት ለመሞከር  የሚጠሩ አካላት ሲመለከቱ ለመንግስት በመጠቆም የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡ የወረዳው አርሶ አደር ግዛው አበረ ለውጡን  ለማጓተት የሚጥሩና  ፀረ የመደመር ኃይሎችን እንቅስቃሴ ለመግታት ከመንግስት ጎን በመቆም ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም