የፀጥታ መዋቅሩን ችግር በማስተካከል የክልሉን ሰላም አስተማማኝ ይደረጋል

69
አሶሳ ሀምሌ 10/2010 በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፀጥታ መዋቅር ውስጥ ያለውን የአደረጃጀትና የመልካም አስተዳደር ችግር በማስተካከል የክልሉን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ እንደሚሰራ ተጠቆመ፡፡ የክልሉ መደበኛ ልዩ ኃይልና አድማ ብተና ፓሊስ አመራሮች በክልሉ ተከስቶ የነበረውን የፀጥታ ችግር ከመቆጣጠር አንፃር በፓሊስ መዋቅሩ የነበረውን ክፍተት የገመገሙበት መድረክ ዛሬ ተጠናቋል፡፡ በግምገማ መድረኩ ላይ መነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የፀጥታ ዘርፍ አማካሪ አቶ አለባቸው ጊዳ “የስነምግባር ችግር ባለባቸው የክልሉ የፓሊስ አባላት ምክንያት ህዝቡ በፓሊስ ተቋም ላይ አመኔታው እየቀነሰ መጥቷል'' ብለዋል፡፡ በፓሊስ መዋቅሩ የሚስተዋሉ የአሰራርና የመልካም አስተዳደር ችግሮች የፈጠሩትን ቅሬታ ለማስተካከል አደረጃጀቱና አሰራሩ ሊፈተሽ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተደድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው በክልሉ የተከሰተው የፀጥታ ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ችግሩ ከመከሰቱ በፊት የተስተዋሉ ፍንጮች ቢኖሩም የፀጥታ መዋቅሩ ቀድሞ የመከላከል ሥራ እንዳላከናወነ ገልጸዋል፡፡ “የፀጥታ ችግሩ ከተከሰተ በኋላም የጸጥታ መዋቅሩ ፈጥኖ ለመቆጣጠር ያደረገው እንቅስቃሴም ደካማ ነበር'' ብለዋል አቶ አሻድሊ፡፡ የፀጥታ ችግሩን ለመቆጣጠር ገለልተኛ ሆኖ ከመስራት ይልቅ ለአንድ ወገን በማድላት በግጭቱ የተሳተፉ የፓሊስ አባላት መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡ የፓሊስ አባላትን ጨምሮ በግጭቱ የተሳተፉ አካላት ላይ የተጀመረው ማጣራት ቀጣይ እንደሚሆንና ተገቢው ህጋዊ እርምጃም እንደሚወሰድም አስታውቀዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት በክልሉ ፓሊስ መዋቅር የተጠቀሱት ችግሮች ያለባቸው አባላት ቢኖሩም ተቋሙ ህዝባዊነት እንደሌለው ተደርጎ የተሳሳተ መረጃ የሚያሰራጩ አካላት አሉ፡፡ የፓሊስ መዋቅሩ በክልሉ የሚኖሩ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ተወላጆችን ያካተተ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የክልሉ አስተዳደርና ፀጥታ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሳ አህመድ “በክልሉ ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር የክልሉን የፓሊስ መዋቅር በቀጣይ ሊደራጅበት የሚገባውን መንገድ አመልክቷል'' ብለዋል፡፡ በፓሊስ መዋቅሩ የተስተዋለውን ችግር ለማስተካከል ተመሳሳይ ግምገማ በየደረጃው ባሉ የፀጥታ አካላት እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡ የፓሊስ መዋቅሩ ችግሩን በአጭር ጊዜ አርሞ የክልሉን ህዝብ ይቅርታ በመጠየቅ በህዝቦች መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡                        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም